የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዋልያ ቢራ ጋር አዲስ የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ተፈራረመ

አርባ ስምንት ደቂቃዎችን ዘግይቶ በጀመረው ፕሮግራም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን እና ዋሊያ ቢራ አክስዮን ማህበርን ወክለው የኢትዮጵያ እግር ኳሰ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ፣ የሄኒከን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዬጂን እንዲሁም ሌሎች የሁለቱ ተቋማት የበላይ አመራሮች በመገኘት የፊርማ ስነ- ስርዓት አከናውነዋል። አመራሮቹም ስለ ስምምነቱ ገለፃ አድርገዋል።

የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ዝግጅቱን ያስጀመሩት አቶ ኢሳይያስ ጂራ አርፍደው በመምጣታቸው ይቅርታ ጠይቀው ስለ ስፖንሰር ሺፑ ገለፃ አድርገዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ዋሊያ ቢራ የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለመደገፍ ቆርጦ ስለመጣ አመስገንው ” ስምምነቱ እነሱ ከዚህ ቀደም የሚያገኙትን ጥቅም የሚያሳጣቸው ነው። ነገር ግን እግር ኳሳችንን ለመደገፍ ቆርጠው ስለተነሱ በጣም የሚያስመሰግናቸው ነው።” ያሉት አቶ ኢሳይያስ ጨምረው ሲያስረዱ “የእኛ እና የዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማህበር የብቸኛ ስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በዋናነት የምግብ እና መጠጥን አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ መሰረት አድርጎ ለመስራት እና በተመሳሳይ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም ለማስጠበቅ ግዴታ እና መብትን በግልፅ የሚያሳይ እንዲሆን ተደርጎ የተሰራ ነው።” በማለት ስለ ስምምነቱ እና ስለወጣው አዋጅ አስረድተዋል።

ከጥር 1 ቀን 2019 እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2022 በሚቆየው ይህ የአራት ዓመት ስምምነት እንደ ከዚህ ቀደሙ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሄራዊ ቡድንን (ዋሊያዎቹ) ብቻ የሚመለከት አለመሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹን) እንደሚመለከት ተናግረዋል። በስምምነቱ መሰረት የዋሊያ ቢራን ምርት የሚያስተዋውቅ ምስል ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች በልምምድ ሜዳ ላይ በሚያደርጉት ማሊያ፣ ቱታ፣ ቦርሳ እና ተያያዥ መገልገያዎች ላይ እንደሚለጠፍ የገለፁት አቶ ኢሳይያስ እነሱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዝርዝር ጉዳዮች ሰሞኑን ከሚወጣው የአዋጅ አፈፃፀም በኋላ ተጨማሪ ነገሮች እንደሚካተቱ ጠቁመዋል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

አራት ወራት እንደፈጀ በተነገረለት ድርድር ላይ ብሄራዊ ፌደሬሽኑ መጀመሪያ ከተቋሙ (ከዋሊያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር) በቀረበለት ፕሮፖዛል ላይ ማሻሻያዎችን እንዳደረገ እና መጀመሪያ በቀረበለት የገንዘብ ሁኔታ እንዳልተስማማ በመግለጫው ሲገለፅ በተለይ በአራቱ ወራት ሁለቱን ወገኖች ተጠቃሚ በሚያደርግ ሁኔታ ስራዎች እንደተሰሩ ተብራርቷል።

በየሶስት ወሩ 3.5 ሚሊየን ብር ዋሊያ ቢራ ለብሄራዊ ፌደሬሽኑ እንደሚከፍል በመጨረሻ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በአጠቃላይ በአራት ዓመት ፌደሬሽኑ ከዋሊያ ቢራ 56 ሚሊዮን ብር እንደሚያገኝ አስረድተዋል።

ከአቶ ኢሳይያስ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የሄኒከን ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዮጂን በስምምነቱ ደስተኛ እንደሆኑ አስረድተዋል። “እዚህ በመገኘታችን እና ስምምነቱን በማድረጋችን በጣም ደስተኞች ነን። እኛ የኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ብሄራዊ ቡድኖችን ስፖንሰር እንድናደርግ በመደረጉ እድለኞች ነን ምክንያቱም እኛ የወደፉት ራዕይ አለን ከሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ማደግ እንፈልጋለን።” በማለት የተሰማቸውን ስሜት አጋርተዋል።

ከሁለቱ አካላት ንግግር በኋላ የፊርማ ስነስርዓት የተደረገ ሲሆን ከብዙሃን መገናኛዎች በተነሱ ማብራሪያ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር መግለጫ ተሰጥቷል።

ስለ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር አዋጅ እና ስምምነቱ፣ ስለ ስፖንሰር አድራጊው ተቋም ተጠቃሚነት እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ መስጠጥ የተጀመረ ሲሆን በተለይ ስለስምምነቱ ዝርዝር ጉዳዮች በመጠኑ ተብራርተዋል።

ከማብራሪያው በኋላ የኬክ መቁረስ ስነ-ስርዓት የተከናወነ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ለሄኒከን ኢትዮጵያ የኳስ ስጦታ ማበርከቱ ታይቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *