ሪፖርት | የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው ነጥብ ተጋርቶ የማለፍ ዕድሉ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

በቶኪዮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2020 የኦሎምፒክ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች (የኦሊምፒክ) ብሔራዊ ቡድን የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኖ አንድ አቻ ተለያይቷል።

በናምቢያዊው ጃክሰን ፓቫሳ የመሃል ዳኝነት በተመራው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ ፉክክር ሲስተዋልበት በተቃራኒው በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ታይቶበታል። በ4-3-3 የተጨዋች አደራደር የገቡት አብርሃም መብራቱ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ ቢስተዋልም ተጋባዦቹ ማሊዎች በመረጡት የመከላከል አጨዋወት ምክንያት ለጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች ክፍተት ባለማግኘታቸው አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ኳስን ሲቀባበሉ ውለዋል። በተቃራኒው ከሜዳቸው ውጪ እንደመጫወታቸው የአቻ ውጤትን እንደሚፈልጉ በሚያሳብቅ ሁኔታ ወደ ኋላ አፈግፍገው የተጫወቱት ማሊዎች በ4-4-2 የጨዋታ ፎርሜሽን ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፍጥነት የተሞላበት አጨዋወት ያስመለከቱት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ቶሎ ቶሎ ወደ ማሊዎች የግብ ክልል በመድረስ ሙከራ ማድረግ ጀምረዋል። በ7ኛው ደቂቃም የቡድኑ የግራ መስመር ተከላካይ ደስታ ዮሐንስ ከቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር በመሞከር የማሊዎችን ግብ ገና በጊዜ መፈተሽ ጀምሯል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከነዓን ማርክነህ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ በመታው ኳስ ሌላ ሙከራ ማድረግ የቻሉት የአብርሃም ተጨዋቾች ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ኳስን አደራጅቶ ለመውጣት ሲሞክር የተስተዋለው የቡድኑ አምበል አማኑኤል ዮሐንስ በ18ኛው ደቂቃ ከከነዓን ጋር ጥሩ አንድ ሁለት ተቀባብለው ለደስታ ዮሐንስ በማቀበል ሌላ ሙከራ በደስታ አማካኝነት ቢያደርጉም መክኖባቸዋል።

በቁጥርም ሆነ በአካላዊ አቋም ብልጫ የተወሰደባቸው የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በ19 እና በ22ኛው ደቂቃ ከርቀት እየመቱ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ከሁለቱ ሙከራዎች በተጨማሪ በ25ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አልካሊፋ ኩሊባሊ ሲተፋው አቡበከር ተገልብጦ ለማስቆጠር ሞክሮ ወደ ውጪ ወቶበታል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ተጋጣሚያቸው ኳስን ከኋላ መስርቶ እንዳይወጣ ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ማሊዎች ከዚህኛው ደቂቃ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ራሳቸው ግብ ተጠግተው ክፍተቶችን ለመዝጋት ጥረዋል። በክፍት ጨዋታ ወደ ማሊዎች የግብ ክልል መድረስ የተሳናቸው የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ግብ ለማግባት ረጃጅም ኳሶችን ቀላቅለው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በዚህም በ35ኛው ደቂቃ ከርቀት በተሻማ ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ግብ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጥሩ አጋጣሚ ያገኙት ማሊዎች በቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት መሪ ሆነው ወደ እረፍት ሊያመሩ የሚችሉበትን አጋጣሚ አምክነዋል።

የቀድሞው የፌስቡክ ገፃችን ለጊዜው በኛ ቁጥጥር ስር የማይገኝ በመሆኑ አዲሱ ገፃችንን ሊንኩን በመከተል ላይ ያድርጉ – facebook.com/SoccerEthiopia

ከእረፍት መልስ መልኩን ለውጦ የመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ከጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ጋር አስመልክቷል። በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ተሽለው የቀረቡት የአብርሃም ተጨዋቾች አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የማሊዎች ሜዳ ላይ በማሳለፍ ተንቀሳቅሰዋል። በተቃራኒው ከመጀመሪያው አጋማሽ ይበልጥ በመከላከሉ ተጠምደው ያሳለፉት ማሊዎች በመልሶ ማጥቃት ከሚሰነዝሩት አስደንጋጭ ሙከራዎች ውጪ አጨዋወታቸውን ገድበው ተንቀሳቅሰዋል። ከመልሶ ማጥቃት ውጪ የቆሙ ኳሶችንም ለመጠቀም የፈለጉት ማሊዎች በ50ኛው እና በ52ኛው ደቂቃ ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ከመዓዘን ምት በአምበላቸው ዮሱፍ ትራዩሬ እና ሲያካ ባካዮኮ አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል። በእነዚህ ሁለት ሙከራዎች የተደናገጡ የሚመስሉት የኢትዮጵያ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች በ53ኛው ደቂቃ በፈጠሩት የትኩረት ማነስ ስህተት ዴያዴ ዲያንካ ግብ አስቆጥሮባቸው መመራት ጀምረዋል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በሙሉ ኃይላቸው ማጥቃት የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ከተለያዩ አማራቾች ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ከግቡ መቆጠር ሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቡበከር ናስር ከከንዓን ጥሩ ኳስ ተቀብሎ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ቢጥርም ሙከራው ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የማጥቃት ኃይላቸውን በመጨመር እና የአማካይ ክፍሉን ጥምረት በማስተካከል ይበልጥ ተጭነው ተጫውተዋል። በዚህም ሱራፌል ዳኛቸውን ቀይሮ የገባው አፈወርቅ ኃይሉ የጨዋታውን መልክ በመቀየር ቡድኑ ወደ ፊት እንዲሄድ ሲረዳ ተስተውሏል። በ67ኛው ደቂቃም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከአብዱላይ ዲያቤ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ለከነዓን አሻግሮለት ብሄራዊ ቡድኑ ጥርት ያለ የግብ ማግባት እድል የፈጠረ ሲሆን አማኑኤል ያሻማውን ኳስ ከነዓን በግምባሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው አልካሊፋ ኩሊባሊ አምክኖታል።

አሁንም ጫና ማሰደራቸውን የቀጠሉት ተጨዋቾቹ በ74ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ግብ አስቆጥረዋል። በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ደስታ ደሙ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ነበር በግምባሩ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ያደረገው። አቻ ከሆኑ በኋላም ግብ ለማስቆጠር ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በተለይ ለአብዱሌይ ዲያቤ ፈተና ሆኖ ባመሸው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጥሩ ጥሩ እድሎችን ሲፈጥሩ ታይቷል።

በ87ኛው ደቂቃ ከእስራኤል እሸቱ ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን ተጨዋቹ ወደ ግብ የመታው ኳስ ፊት ለፊት በመሆኑ ግብ ጠባቂው አምክኖታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በአስደንጋጭ መልሶ ማጥቃት ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የደረሱት ማሊዎች ግብ አስቆጥረው መሪ ሊሆኑበት የሚችሉበትን እድል ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። የአቻ ውጤት እንደሚጎዳቸው የተረዱት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በጭማሪ ሰዓት የጨዋታው የመጨረሻ እድል በእስራኤል አማካኝነት ፈጥረው ተከላካዮች አምክነውባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ 1ለ1 ተጠናቋል።

የመልሱ ጨዋታ በቀጣይ ማክሰኞ ባማኮ ላይ የሚደረግ ሲሆን በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን በቀጣዩ የማጣርያ ዙር ካሜሩንን ይገጥማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *