ካካሜጋ ላይ ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ዩጋንዳ ደቡብ ሱዳንን 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የምድብ ሁለትን መሪነት ከቡሩንዲ ነጥቃለች፡፡ ዩጋንዳ ብዙ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ብልጫን ወስዳ የተጫወተች ሲሆን ከሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ውጪ መሆኗን ያረጋገጠችው ደቡብ ሱዳን በበኩሏ ከኢትዮጵያ ጋር ከተጫዋተችው በተሻለ ወደ ግብ በመድረስ እና ሙከራ በማድረግ ተሻሽለው ታይተዋል፡፡
ዩጋንዳ በመጀመሪያው ጨዋታ ነጥብ መጣሏን ተከትሎ ሙሉ ሶስት ነጥብ እና ቡዙ ግብ ለማስቆጠር ከጨዋታው መጀመሪያ ነበር የማጥቃት እንቅስቃሴዋን ያጠናከረችው፡፡ ከሁለቱ የመሃል ተከላካዮች በስተቀርም አብዛኞቹ ተጫዋቾች በተጋጣሚ የሜዳ ክልል እየተገኙ ጫናን ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡ ክሬንሶቹ በ10 ደቂቃ ውስጥ አከታትለው ያስቆጠሯቸው ግቦች 2-0 እንዲመሩ አስችሏቸዋል፡፡ ሁለቱም ግቦች ሲቆጠሩ ኳስ የተነሳቸው ከግራ መስመር ነበር፡፡ ሚልተን ካሪሳ በ7ኛው ደቂቃ የደቡብ ሱዳን ተከላካዮች የመከላከል ስህተትን ተጠቅሞ ዩጋንዳን መሪ ሲያደርግ ሁድ ካዌሳ ከሶስት ደቂቃ በኃላ በግንባሩ በመግጨት ልዩነቱን አስፍቷል፡፡ ደቡብ ሱዳኖች የዩጋንዳ ተከላካይ ክፍል በተለይም የመስመር ተከላካዮች ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርጉት የዘገመ ሽግግር ምከንያት ግብ ማስቆጠር የሚችሉባቸውን እድሎች ሲያገኙ ነበር፡፡ በተለይ በዩጋንዳ የግራ መስመር ላይ የመከላካል ድክመት መኖሩን ተክትሎ የተገኘውን እድል ሉክ ዎል ተጠቅሞ ልዩነቱን ወደ አንድ ሲያጠብ ከአራት ደቂቃ በኃላ ዴሪክ ንሲምባቢ በግሩም ሁኔታ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን ጁማ ጂናሮን ጭምር በማቆም ከመረብ ላይ አርፋለች፡፡
ዩጋንዳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ትንሽ መቀዛቀዝ ቢታይባቸውም ግብ ከማስቆጠር ግን አላገዳቸውም፡፡ ንሲምባቢ ለራሱ ሁለተኛው እንዲሁም ለሃገሩ አራተኛውን ግብ ከማዕዘን የተሻረገ ኳስ ተጠቅሞ በ58ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በ85ኛው ደቂቃ ኒኮላስ ዋዳዳ አምስተኛውን አክሏል፡፡
ምድብ ሁለትን ዩጋንዳ በአራት ነጥብ እና በአራት ግብ ስትመራ ቡሩንዲ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ሁለተኛ ነች፡፡ ኢትዮጵያ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ ስትሆን በመጪው እሁድ ከዩጋንዳ ጋር በቡኩንጉ ስታዲየም ትጫወታለች፡፡
የዛሬ ጨዋታ ውጤት
ዩጋንዳ 5-1 ደቡብ ሱዳን
ቅዳሜ ህዳር 30
8፡00 – ሩዋንዳ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)
10፡00 – ኬንያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)
እሁድ ታህሳስ 1
9፡00 – ኢትዮጵያ ከ ዩጋንዳ (ካካሜጋ)
ሰኞ ታህሳስ 2
8፡00 – ሊቢያ ከ ዛንዚባር (ማቻኮስ)
9፡00 – ደቡብ ሱዳን ከ ቡሩንዲ (ካካሜጋ)
10፡00 – ኬንያ ከ ታንዛኒያ (ማቻኮስ)