ፕሪሚየር ሊግ – ደደቢት ወደ መሪነት ተመለሰ

ከእሁድ የቀጠሉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ደደቢት ወደ መሪነት የተመለሰበትን ፣ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከመጨረሻው ደረጃ ያንሰራራበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡

በ9 ሰአት ወላይታ ድቻን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናገደው ደደቢት 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ሊጉ መሪነት ተመልሷል፡፡ ደደቢት ሳሚ ሳኑሚ እና መስፍን ኪዳኔ ባስቆጠሩት ግቦች 2-0 ቢመራም ወላይታ ድቻዎች አላዛር ፋሲካ አከታትሎ ባስቆጠራቸው ግቦች የመጀመርያውን አጋማሽ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ በመጨረሻም ከእረፍት መልስ በ63ኛው ደቂቃ በድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ሳሚ ሳኑሚ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ሰማያዊውን ጦር ለድል አብቅቷል፡፡

ደደቢት ድሉን ተከትሎ ከ3 ጨዋታ ሙሉ 9 ነጥቦችን አግኝቶ የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጧል፡፡ ድቻ በበኩሉ በ1 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ተረክቧል፡፡

የደደቢት እና ድቻ ጨዋታን ተከትሎ 11፡30 ላይ በተካሄደው ጨዋታ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ፈረሰኞቹ ሲሆኑ በ9ኛው ደቂቃ አምበሉ ደጉ ደበበ የመታው ቅጣት ምት በግቡ አግዳሚ ሲመለስ ሳላዲን በርጊቾ አግኝቷት ግብ አድርጓታል፡፡ መከላከያዎችን አቻ ያደረገችውን ግብ ያስቆጠረው በሁለተኛው አጋማሽ በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው መሃመድ ናስር በቅጣት ምት ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲሱ የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 3 ጨዋታዎች ሁለቱን በአቻ ውጤት አጠናቆና አንድ ጨዋታ አሸንፎ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ጎንደር ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ2-1 ተሸንፏል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ቢንያም አሰፋ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ሲያስቆጥር የተሻ ግዛው ዳሽንን አቻ የምታደርግ ግብ በ63ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና የማሸነፍያ ግብ የተቆጠረችው በ75ኛው ደቂቃ ሲሆን ቢንያም አሰፋ ወደ ግብ የመታው ኳስ በዳሽን ተከላካይ ተጨርፋ ወደ ግብነት ተቀይራለች፡፡

ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ከወራጅ ቀጠናው በመጠኑ የተላቀቀ ሲሆን ዳሽን ቢራ ዘንድሮ ያደረጋቸውን 2 የሜዳው ጨዋታዎችን በሽንፈት አጠናቋል፡፡

ሊጉን ደደቢት በ9 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና በ8 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ6 ይከተላሉ፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሁለቱ ናይጄርያውያን ሳሚ ሳኑሚ እና ፊሊፕ ዳውዚ በ6 እና በ3 ግቦች የመጀመርያዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

ያጋሩ