ነገ ከሚደረጉ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ሽረ እና ባህር ዳርን የሚያገናኘውን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።
ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ስሑል ሽረዎች ነገ 09፡00 ላይ በአምስተኛነት የተቀመጠው ባህር ዳር ከተማን ያስተናግዳሉ። የዛሬውን የደቡብ ፖሊስ ድል ተከትሎ በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ላይ የሚኖረው ፉክክር ይበልጥ ከባድ የሚሆንባቸው ሽረዎች ነገ ሙሉ ነጥቦችን ለማሳካት ይገደዳሉ። ሁለተኛውን የውድድር አጋማሽ ዘጠነኛ የአቻ ውጤታቻውን በማስመዝገብ የጀመሩት ሽረዎች ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ማገገማቸው እና ከሜዳ ውጪ አንድ ነጥብ ማሳካት መቻላቸው በመጠኑም ቢሆን መነቃቃትን የሚፈጥርላቸው ነው። ቡድኑ በነገው ጨዋታም ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ባሳላፍነው ሳምንት በመኖሪያ ፍቃድ አለመሟላት ምክንያት ያላሰላፋቸውን ተጫዋቾችንም እንደሚጠቀም ይጠበቃል። በመሆኑም አዲስ ፈራሚዎቹ ጋይሳ አፖንግ እና ሳሊፉ ፎፋና በመጀሪያው አስተላለፍ ውስጥ የመካተት እድል ይኖራቸዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስን ለሁለተኛ ጊዜ ድል በማድረግ ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ ነጥባቸውን 25 ማድረስ ችለዋል። አንድ ነጥብ ብቻ ካሳኩባቸው የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ድል ማስመዝገባቸው በሊጉ አናት ከሚገኙ ክለቦች ጋር እንዳይራራቁ ከማስቻሉ በላይ መልካም ወደ ነበረው የዓመቱ አጀማመራቸው ለመመለስም የሚረዳቸው ነው። ሆኖም ባህር ዳሮች የነገው ጨዋታ እንዲከብድባቸው የሚያደርገው ወደ ሽረ ይዘው የተጓዙት ስብስብ ጥልቀት አናሳነት በመሆኑ ነው። በዚህም ቡድኑ አስናቀ ሞገስ ፣ ኤልያስ አህመድ ፣ ቴዎድሮስ ሙላት ፣ ተስፋሁን ሸጋው እና ዜናው ፈረደን በጉዳት ወንድሜነህ ደረጄ እና ምንተስኖት አሎን በኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ እንዲሁም ከክለቡ ሊለያዩ ከጫፍ የደረሱት ታዲዮስ ወልዴ እና አህመድ ቢን ዋታራ ሳያካትት ነው ስሐል ሽረን የሚገጥመው።
የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች
– ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በፍቃዱ ወርቁ እና እንዳለ ደባልቄ ግቦች 2-0 ማሸነፍ ችሏል።
– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ተመልሷል።
– ስሑል ሽረዎች በሜዳቸው በሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ሲጋሩ አንዴ ደግሞ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
ዳኛ
– ጨዋታውን ማኑኄ ወልደፃዲቅ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው አራት ጨዋታዎች 12 የቢጫ ካርዶችን ሲመዝ አራት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ሰንደይ ሮቲሚ
አብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ረመዳን ዮሴፍ
አሳሪ አልመሐዲ– ደሳለኝ ደበሽ
ሳሊፉ ፎፋና – ያስር ሙገርዋ – ጋይሳ አፖንግ
ቢስማርክ አፒያ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ሐሪሰን ሄሱ
ሣለአምላክ ተገኝ – አሌክስ አሙዙ – አቤል ውዱ – ሄኖክ አቻምየለህ
ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ዳግማዊ ሙሉጌታ
ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡