የአንደኛ ዙር ግምገማ አይካሄድም
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር የሁለተኛው ዙር ነገ እንደሚጀመር ሲጠበቅ በውድድሩ አጋማሽ ላይ ይደረግ የነበረው የ1ኛ ዙር ግምገማ ይዘቱን በመለወጥ መጠይቃዊ እንዲሆን ተደርጓል። በቡድን አመራሮች የሚሞላው መጠይቅ ወደ 36 ቡድኖች የተላከ ሲሆን የሚሰጡት ምላሾችን መሰረት በማድረግ ጥናታዊ ፅሁፍ የሚዘጋጅ ይሆናል።
ዝውውሮች
በዚህ ዘገባ በምድቦቹ አናት ላይ የሚገኙትን ቡድኖች ብቻ እንመለከታለን። (ያልተጠቀሱ ቡድኖች ተጫዋች አላስፈረሙም)
– የምድብ ሀ የምድብ መሪ መሆን የቻለው ሰበታ ከተማ የቀድሞ አጥቂው ዐብይ ቡልቲን ከወልዲያ መልሰው ሲያስፈርሙ ኃይለሚካኤል አደፍርስን ከወጣት ቡድን አሳድገዋል።
– በሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የፊት መስመራቸው ላይ አንድ ተጨማሪ ተጫዋች ማካተት ችለዋል። ዘንድሮ በቢሾፍቱ አውቶሞቲቪ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ወንድምአገኝ አብሬ የቡድኑ ብቸኛ ፈራሚ ነው።
– በምድብ ለ በግብ ክፍያ መድንን በመብለጥ መሪነት ላይ የተቀመጠው ወልቂጤ ከተማ አምስት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ከደደቢት የለቀቀው አክዌር ቻም፣ የቀድሞ አጥቂው መሐመድ ናስርን ከስልጤ ወራቤ፣ በዚህ ውድድር ዓመት በወለይታ ሶዶ ድንቅ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው ዳግማዊ ሰለሞን፣ የአክሱም ከተማው ቢንያም ጌታቸው እንዲሁም የናሽናል ሴሜንቱ ግብ ጠባቂ የነበረው ሀምዲ ወደ ወልቂጤ ያመሩ ተጫዋቾች ናቸው።
– ኢኮስኮ ከኢትዮጵያ መድን ታምሩ ባልቻን እንዲሁም ኤርምያስ ኃይሉን ከአውስኮድ ሲያስፈርም የ4 ተጫውቾችን ውል አራዝሟል።
በምድብ ሐ የምድቡ መሪ የሆነው ሀድያ ሆሳዕና በዘንድሮ ውድድር ዓመት አዳማ ከተማ ሲጫወት የነበረው ሱራፌል ጌታቸውን ወደ ቡድኑ ሲቀላቅል ዕርቅይሁን ተስፋዬ የቀድሞ ቡድኑንን መልሶ ተቀላቅሏል። የቀድሞ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋች አየለ ተስፋዬ ሌላው የቡድኑ ፈራሚ ነው።
የቡድኖች ቅሬታ
የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል የምድብ ሀ እና ለ ጨዋታዎች በ14 እና 15 እንደሚጀምሩ መርሐ ግብር ቢያወጣም አንዳድንድ ቡድኖች ባጋጠማቸው ችግር ይራዘምልኝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ቅሬታዎች ከየቡድኖቹ እየተሰማ ይገኛል። በተለይም በምድብ ለ የዲላ ከተማ፣ ድሬዳዎ ፖሊስ እና ሀምበሪቾ ይራዘምልኝ ጥያቄ ተጋጣሚዎቻቸውን ቅሬታ ውስጥ ከትቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ስራ ሲኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ‘ በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታ መራዘሙ ምንም አግባብነት የለውም። በሜዳችን ተጫውተን ቀጣይ ያለውን ጨዋታ ወጥተን መጫወት ነው ያለብን። በምንም አይነት ምክንያት ውድድሩ መራዘም የለበትም። ውድድር መራዘም ያለበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ የአውስኮድ እና የዲላ ምክንያት ማንኛውንም አካል የሚሳምን ነው። ከዚያ ውጭ አሳማኝ አይደለም፤ ይህን ቅሬታችንን ከንቲባ ቢሮ ድረስ አስገብተናል። ከውድድሩ ራሳችንን ማግለል ድረስ የሚደርስ ነገር ነው ።”ብለዋል።
ኢኮስኮዎች በበኩላቸው ” በአካል ሄደን አጣርተን መሄድ እንደምንችል ተነግሮናል። ለዛም ይሆን ዘንድ የጉዞ ቲኬት ቆርጠን ቀድመን ዝግጅት የጀመርን ስለሆነ አወዳዳሪው አካል የፕሮግራም ለውጥ ማድረግ የለበትም። ሁሉም ቡድኖች የመንግስት እና የድርጅት ገንዘብ ነው የሚጠቀሙበት። ዘንድሮ በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነበር። ገና ሁለተኛ ዙር ላይ እንዲህ ከሆነ ወደ መሐል ስንደርስ ያለውን ማሰብ ቀላል ነው።”
የአቶ ኢብራሂም ማሐመድ (የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ) ምላሽ
” ማንኛውንም ውድድር በሰዓቱ እና በጌዜው ነው ማከናወን የምንፈልገው። ማንንም ለመጥቀም ሆን ብለን ያደረግነው አይደለም። የተራዘሙት ጨዋታዋች በሙሉ ምክንያት አላቸው። አውስኮድ ፈርሶ መቋቋም ላይ ስለሆነ፣ ዲላ በተፈናቀሉት ወገኖች ላይ ስፖርተኛው ተሳታፊ ስለሆነ፣ እንዲሁም ድሬዳዎ ፖሊስ የቡድኑ አባላቶች በአከባቢው ያለውን ፀጥታ ቅድሚያ በመስጠት እየተሳተፉ ስላሉ እና ሀምበሪቾ የአመራር ሹም ሽር እያደረገ ስለሚገኝ ክፍተት ተፈጥሮ የፀጥታ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት ስላለ ነው። በታቸልን መጠን ፍትሀዊ ሆነን ለመስራት እንሞክራለን።
የዚህ ሳምንት ጨዋታዎች (12ኛ ሳምንት)
ቅዳሜ መጋቢት 14
አውስኮድ PP ፌዴራል ፖሊስ
እሁድ መጋቢት 15
አክሱም ከተማ 9:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ወሎ ኮምበልቻ 9:00 ሰበታ ከተማ
ወልዲያ 9:00 አቃቂ ቃሊቲ
ለገጣፎ ለገዳዲ 9:00 ገላን ከተማ
ደሴ ከተማ 9:00 ቡራዩ ከተማ
ምድብ ለ
እሁድ መጋቢት 15
ኢትዮጵያ መድን 9:00 ነገሌ አርሲ
ሀላባ ከተማ 9:00 ናሽናል ሴሜንት
የካ ክ/ከተማ 9:00 ወልቂጤ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ PP ድሬዳዎ ፖሊስ
ሀምበሪቾ ዱራሜ PP ኢኮስኮ
ወላይታ ሶዶ PP ዲላ ከተማ
ምድብ ሐ (በዚህ ሳምንት የለም)
እሁድ መጋቢት 22
ካፋ ቡና 09:00 ሻሸመኔ ከተማ
ቡታጅራ ከተማ 09:00 ነጌሌ ቦረና
ቤንች ማጂ ቡና 09:00 ነቀምት ከተማ
ስልጤ ወራቤ 09:00 ሀዲያ ሆሳዕና
ጅማ አባ ቡና 09:00 ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ
አርባምንጭ ከተማ 09:00 ሺንሺቾ ከተማ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡