በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ገጥሞ ተቀይሮ በገባው ሄኖክ አየለ ብቸኛ ጎል አራተኛ ተከታታይ ድል አግኝቷል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ደቡብ ፖሊሶች በ16 ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ መከላከያን በረቱበት ወቅት ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾችን ቅያሪን አድርገው ሄኖክ አየለ እና ብሩክ አየለን ወደ ተጠባባቂ ወንበር በማውረድ በኃይሉ ወገኔ እና ኪዳኔ አሰፋን አስገብተዋል። በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማም ኢትዮጵያ ቡናን በሜዳው በረታበት ወቅት ከተጠቀመው አሰላለፍ በረከት ሳሙኤልን በቅጣት፣ ኤታሙና ኬይሙኒን በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት በማጣታቸው ፍሬድ ሙሸንዲ እና ኤልያስን ማሞን በምትካቸው ተጠቅመዋል፡፡
ፌድራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በመሩት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቡብ ፖሊሶች በእንቅስቃሴ እና በሙከራ ረገድ የተሻሉ ሆነው የታዩበት ድሬዳዋ ከተማዎች ከመሀል ሜዳ ሊዘል ያልቻለ እና የጠራ የግብ ማግባት ሙከራን ማድረግ ያልቻሉበት ነበር፡፡ 11ኛው ደቂቃ የቀድሞው ቡድኑን በተቃራኒው የገጠመው እና ልዩነት ፈጣሪ በመሆን ለደቡብ ፖሊሶች ጥሩ መሆን ጉልህ ድርሻ የነበረው ዘላለም ኢሳይያስ ከበኃይሉ ወገኔ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ያሻገረውን የተሻ ግዛው ሲመታው ዘነበ ከበደ ተደርቦ አስጥሎታል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ በድጋሚ በቀኝ የድሬዳዋ የግብ ክልል የተሻ በረጅሙ ያሻገራትን ኳስ በኃይሉ ወደ ግብ ሳትበርድ ቢለጋትም ሳምሶን አሰፋ ይዞበታል፡፡
የደስታ ጊቻሞንና እና የጋናዊውን ተከላካዮችን ጥምረት ሰብሮ ለመግባት የተቸገሩት ድሬዳዎች ሐብታሙ ወልዴን በብቸኛ የፊት አጥቂነት በመጠቀም ብዙውን ጊዜያቸውን ኳስን ወደ ግራ እና ቀኝ በመጣል በራምኬል እና ረመዳን ናስር ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት እምብዛም ስኬታማ አልነበረም። ረመዳን ከመሀል ሜዳ በረጅሙ ወደ ግብ በግል ጥረቱ ከሞከራት እና ኢላማዋን ሳትጠብቅ ከወጣችሁ አጋጣሚ ውጪም የጠራ የግብ እድሎችን በመፍጠሩ ስኬታማዎች አልነበሩም፡፡ በአንፃሩ ቢጫ ለባሾች በርከት ያሉ ዕድሎችን እያገኙ ወደ ግብነት ለመለወጥ በሚያደርጉት ሽግግር ግን ፍሬያማ መሆን አልቻሉም፡፡ 19ኛው ደቂቃ ኪዳኔ አሰፋ ከማዕዘን ሲያሻማ አዳሙ መሐመድ በግንባር ገጭቶ የወጣችበት፣ አበባው ቡጣቆ በግራ በኩል በረጅሙ ወደ ድሬዳዋ የግብ ክልል የላካትን ኳስ የድሬዳዋው አንተነህ ተስፋዬ ወደ ራሱ ግብ ገጭቷት ሳምሶን የያዘበት እንዲሁም ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ሲሉ ዮናስ በርታ እና ዘላለም የፈጠሯቸው መልካም አጋጣሚዎች ባለ ሜዳው ብልጫ ለመውሰዱ ማሳያዎች ነበሩ፡፡
በ46ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የድሬዳዋ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ የተገኘችውን የቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ አክርሮ መትቶ በግቡ አግድም በወጣችበት ሙከራ በጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ የምስራቁ ክለብ ከመጀመሪያው አጋማሽ ስህተቱን በማረም ወደ ሜዳ ሲገባ ደቡብ ፖሊሶች ደግሞ በተለይ ሄኖክ አየለ፣ ብሩክ አየለ እና ብርሀኑ በቀለን ያስገቡበት ቅያሪ ስኬታማ ሆኖ በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች እንደ ብልጫቸው ግብ አስቆጥረው አሸናፊ የሆኑበት ነበር፡፡
60ኛው ደቂቃ በረከት ይስሀቅ አመቻችቶ አቀብሎት ኪዳኔ አሰፋ አክርሮ ወደ ግብ ከሳጥን ውጪ ሲመታ ገናናው ረጋሳ ከግቡ ጠርዝ በጭንቅላቱ ገጭቶ ያወጣበት ኳስ ጠንካራ አጋጣሚ ነበረች፡፡ የተሻ ግዛው ከዛም አናጋው በረጅሙ የለጋትን ኳስ በረከት በግንባር ገጭቶ የወጣበትም ሌላው ተጠቃሽ የደቡብ ፖሊስ ሙከራ ነበር።
በ80ኛው ደቂቃ መሐል ሜዳ ላይ ለአራት ደቂቃዎች ያህል ጨዋታ የተቋረጠበት ክስተት ተከስቷል፡፡ ከመሐል ዳኛው ዳንኤል ግርማይ ጋር ግብ ግብ የፈጠረው የደቡብ ፖሊሱ የግራ ተከላካይ አበባው ቡጣቆ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ተጫዋቹ ካርድ ከተመለከተ በኋላ ከሜዳ ለመውጣት ሲያንገራግርም ተመልክተናል፡፡
በጎዶሎ ተጫዋች ቀሪውን ደቂቃ ለመጫወት የተገደዱት ቢጫ ለባሾቹ በበረከት ይስሀቅ እና ዘላለም ኢሳያስ ልዩ ጥምረት ውጤት ይዘው ወጥተዋል፡፡ በ85ኛው ደቂቃ በረከት ይስሀቅ ከዘላለም ኢሳይያስ የተመቻቸለትን ኳስ ገናናው ረጋሳን በማለፍ ሲያሻማ ተቀይሮ የገባው ልማደኛው ሄኖክ አየለ በግንባር በመግጨት ደቡብ ፖሊስን ሙሉ ሶስት ነጥብ ያስጨበጠች ግብ አስቆጥሯል።
ጨዋታው በደቡብ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቢጫ ለባሾቹ ተከታታይ አራተኛ ድል በማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ በፍጥነት መጓዛቸውን ቀጥለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡