የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 4ኛ ሳምንት ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ሲካሄዱ መከላከያ፣ አዳማ ከተማ እና ቅዱሰ ጊዮርጊስ አሸንፈዋል።
በጎፋ ሜዳ 04:00 የጀመረው የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በመከላከያ 6-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመከላከያ የበላይነት በታየበት በዚህ ጨዋታ ጦሩ አጥቂው ምስግናው መላኩ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ጀምረዋል። በማስከተል በቅዱስ ዮሐንስ ሁለተኛ ጎል መምራታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች ከደቂቃዎች በኋላ አስደናቂ ሁለት ጎሎችን ምስግናው መላኩ አስቆጥሮ በሰራው ሐት-ትሪክ የግብ መጠኑን ወደ አራት ከፍ አድርጎታል።
ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ቢችሉም የጎል እድል መፍጠር እና ያገኙትን አጋጣሚ መጠቀም ላይ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ለማየት ችለናል። መከላካያዎች ብልጫ ቢወሰድባቸውም በተከታታይ ወንድይፍራው ወ/ማርያም እና አቤል ሲሳይ ባስቆጠሩት ሁለት ጎሎች የግብ መጠናቸውን ወደ ስድስት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ለኢትዮጵያ ቡና በተጨማሪ ደቂቃ የማስተዛዘኛ ጎል ታምራት ፈለቀ አስቆጥሮ ጨዋታው በመከላከያ 6-1 ሰፊ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
በመከላከያ በኩል አጥቂው ምስግናው መላኩ በጨዋታው ሐት-ትሪክ ከመስራቱም ባሻገር እንቅስቃሴው ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልበት ታዳጊ መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።
በማስከተል 06:00 ላይ ሀሌታ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በአዳማ ከተማ ሦስት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት አዳማዎች ሲሆኑ ፍራኦል ጫላ አስቆጥሮታል። ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ሀሌታዎች በይስሐቅ ብርሃኑ የርቀት ጎል አንድ አቻ በመሆን እረፍት ወጥተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ አዳማዎች ተሽለው መንቀሳቀስ ሲችሉ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ፍራኦል ጫላ አከታትሎ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ የአዳማን የጎል መጠን ወደ ሦስት በማድረስ አዳማዎች 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ እንዲያጠናቅቁ አስችሏል።
በአራተኛ ሳምንት ባስቆጠረው በዚህ ውድድር ፍራኦል ጫላ እስካሁን ሰባት ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራ ይገኛል።
08:00 በጃን ሜዳ በተደረገው ሦስተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣቶች አካዳሚን 4 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ብዙ ተመልካች የተከታተለው እና ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው በዚህ ጨዋታ ፀጋዬ መለሰ ባስቆጠረው ጎል መምራት የጀመሩት ፈረሰኞቹ ብዙም ሳይቆዩ ራሱ ፀጋዬ መለሰ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ነበር ወደ እረፍት ያመሩት።
ወጣቶች አካዳሚ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበት ግልፅ የሆኑ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ መልካም የሆነ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያገኙትን አጋጣሚ በአግባቡ አለመጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በየቦታው ባሉ ጠንካራ ተጨዋቾች የተገነባው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ፀጋዬ መለሰ ወደ ጎልነት በመቀየር ሦስተኛ ጎል ሲያስቆጥር በግሉ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። ከደቂቃዎች በኋላ ሲያ በቀለ አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በፈረሰኞቹ 4 – 0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።
ፀጋዬ መለሰ ጎል የማስቆጠር አቅም እንዳለው ባሳየበት በዚህ ጨዋታ በቀጣይ ክለቡ ተጫዋቹ ላይ ጠንካራ ስራ መስራት ከተቻለ ተተኪ አጥቂ መሆን እንደሚችል ከወዲሁ መናገር ይቻላል።
ውድድሩም ነገ በጃልሜዳ ይቀጥልና 04:00 አፍሮ ፅዮን ከ ኢትዮጵያ መድን፤ 06:00 ኢትዮ ኤሌትሪክ ከ ሠላም የሚጫወቱ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡