የ17ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሳምንቱ መርሃ ግብር የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ዛሬ 11 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተከናውኖ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጎንደር በሽንፈት የተመለሰው ሲዳማ ቡና ወደ ተከላካይ ክፍሉ ያመዘኑ አምስት ቅያሪዎችን አድርጓል። ግሩም አሰፋ ፣ ሰንደይ ሙቱኩ ፣ ዳዊት ተፈራ ፣ ጫላ ተሺታ እና ፀጋዬ ባልቻን ከመጀመሪያ አሰላለፍ በማስወጣትም በምትካቸው ዮናታን ፍሰሀ ፣ ዳግም ንጉሴ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ አዲሱ ተስፋዬ እና መሐመድ ናስርን ተጠቅሟል። በተመሳሳይ በኋላኛው ክፍላቸው ላይ ያሬድ ዳዊት እና ተክሉ ታፈሰን በኄኖክ አርፌጮ እና ደጉ ደበበ የቀየሩት ወላይታ ድቻዎች ነጥብ በጣሉበት የሽረው ጨዋታ ግብ ጠባቂ የነበረው መኳንንት አሸናፊን በታሪክ ጌትነት ሲለውጡ አማካዩ ኃይማኖት ወርቁን አሳርፈው አጥቂው አላዛር ፋሲካን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።
ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር በተስተዋለበት ጨዋታ ግብ የተቆጠረው ገና በጅማሮ ሲሆን በግራ ጥላ ፎቅ በሚገኘው ቦታ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ወንድሜነህ ዓይናለም አሻምቶት ግርማ በቀለ በጥሩ ሁኔታ በግምባሩ በማስቆጠር የሲዳማዎች የጨዋታ ጅማሮ በግብ ተውቧል። ገና በጅምሩ ግብ ያስተናገዱት ድቻዎች ለተቆጠረባቸው ግብ ምላሽ ለመስጠት በተከታታይ የሲዳማዎች የግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም በ4ኛው እና በ6ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ እና ቸርነት ጉግሳ በሞከሯቸው የርቀት ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። አሁንም ግብ ለማስቆጠር ሙከራቸውን የቀጠሉት ድቻዎች ከሁለቱ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሙከራ በተጨማሪ በ11ኛው ደቂቃ ጥሩ ግብ የማግባት እድል ፈጥረው መክኖባቸዋል። በዚህኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ እና አላዛር ፋሲካ አንድ ሁለት ተቀባብለው ሲዳማዎች የግብ ክልል ደርሰው አላዛር የሞከረው ኳስ ሌላ ግብ ለማስቆጠር የሞከሩበት አጋጣሚ ነበር።
በፈጣን ሽግግር ( ከመከላከል ወደ ማጥቃት ) ለመጫወት የሞከሩት ሲዳማዎች ገና በጊዜ ግብ ማስቆጠራቸው ያዘናጋቸው በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ የድቻዎች ግብ ክልል ሲደርሱ አልተስተዋለም። ነገር ግን በ13ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ አዲስ ግደይ ውብሸት ዓለማየሁ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ራሱ መቶት በሙከራ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስመለስ ጥሯል። አሁንም ግብ ለማስቆጠር የታተሩት የጦና ንቦቹ በ21ኛው ደቂቃ አስቆጪ እድል አምልጧቸዋል። አብዱልሰመድ ዓሊ ከርቀት ለባዬ ገዛህኝ ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ከባዬ ጋር ተሻምቶ ሲተፋው ቸርነት ጉግሳ አግኝቶ ወደ ግብ የሞከረው ቢሆንም ተጨዋቹ የመታው ኳስ ኃይል ባለመኖሩ ተከላካዮች አውጥተውበታል።
ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተጨዋቾች በ30ኛው ደቂቃ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ ሆነዋል። ከመስመር ሲሻማ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እና ፈቱዲን ጀማል ሳይግባቡ ተጨራርፎ የለቀቁትን ኳስ በድጋሚ ክለቡን የተቀላቀለው አላዛር ፋሲካ አግኝቶት ግብ አስቆጥሯል። ግብ ካስቆጠሩ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በህብረት ወደ ሲዳማዎች የግብ ክልል የደረሱት ዲቻዎች አላዛር ፋሲካ ለቸርነት ጉግሳ አመቻችቶ ቸርነት ባመከነው ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ገና በጊዜ መሪ እንደመሆናቸው ያልተንቀሳቀሱት ሲዳማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት በፈጠሩት ጥሩ እድል መሪ ለመሆን ተቃርበው መክኖባቸዋል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ ያላስተናገደው የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት በመረጡት የጨዋታ ስልት ተቃኝቶ ተካሂዷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በ4-1-3-2 ፎርሜሽን የተጫወቱት ድቻዎች ከፊት መስመር ከተሰለፉት ሁለቱ አጥቂዎቻቸው አላዛር ፋሲካን ወደ መሃል በመሳብ መሃል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ ወስደው ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በተቃራኒው መጀመሪያ በመረጡት የ4-3-3 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ የቀጠሉት ሲዳማዎች የመሃል ሜዳው ላይ የቁጥር ብልጫ እንዳይወሰድባቸው የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሃል አስጠግተው ተጫውተዋል።
በንፅፅር አሰልቺ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመጀመሪያ መከራ የተደረገው ከ20 ደቂቃዎች በኋላ ነበር። በ65ኛው ደቂቃ ሲዳማዎች ገና በጊዜ ግብ ሲያስቆጥሩ ያቀበለው ወንድሜነህ ዓይናለም ከርቀት በሞከረው ሙከራ የድቻዎችን መረብ ለመፈተሽ ጥረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሄኖክ ከቀኝ መስመር አክርሮ የመታው ኳስ ተጨራርፎ ሲመለስ አላዛር በድጋሚ በግምባሩ ለማስቆጠር በሞከረው ኳስ መሪ ለመሆን የጣሩት ዲቻዎች ጥረታቸውን የሲዳማ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል።
በአቻ ውጤት የቀጠለው ጨዋታው አሁንም አስደንጋጭ ሙከራ ሳያስተናግድ የቀጠለ ሲሆን በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት ሙከራቸውን ከቆሙ እና ከርቀት በሚመቱ ኳሶች በማድረግ ቀጥተኛ አጨዋወትን አስመልክተዋል። በዚህም በ75ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዩሃንስ ከርቀት አክርሮ በመታው ነገር ግን ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ባመከነው ኳስ ሲዳማዎች መሪ ለመሆን ቢጥሩም ሃሳባቸው ሳይሰምር ቀርቷል።
ጨዋታውም ተጨማሪ አስደንጋጭ ሙከራ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማዎች ከሊጉ መሪ መቐለ 70 እንድርታ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ሳያጠቡ ሲወጡ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ከሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ሁለት ደረጃዎችን ከፍ ሊሉበት የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡