በዝውውር መስኮቱ በስፋት በዝውውሩ የተሳተፉት ስሑል ሽረዎች የቀድሞ አስልጣኛቸው በረከት ገብረመድኅንን በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ሲቀጥሩ ክፍሎም ገብረሕይወት እና ናትናኤል ተኽለን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል።
ክፍሎም ገብረሕይወት ያለፈው ዓመት ከሁለተኛው ቡድን አድጎ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ አባል የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት በተለያየ ምክንያት ከዋናው ቡድን ስብስብ ዝርዝር ወጥቶ ቢቆይም በድጋሚ ዋናውን ቡድን ለማገልገል ጥሪ ተደርጎለታል። በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይም በተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጥ ችሏል።
ወደ ዋናው ቡድን ጥሪ የተደረገለት ሌላኛው ተጫዋች ናትናኤል ተኽለ ሲሆን እሱም እንደ ክፍሎም በተመሳሳይ በድጋሚ ወደ ዋናው ቡድን የተመለሰ ተጫዋች ነው።
ስሑል ሽረዎች በቀጣይ ቀናትም ሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን እንደሚያሰድጉ ለማወቅ ተችሏል።
ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ስድስት ዓመታት በምክትል ኣሰልጣኝነት ካገለገለበት ክለብ በስምምነት ተለያይቶ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ያለ ስራ ሀቀምጦ የቆየው ወጣትየቱ አሰልጣኝ በረከት ገብረመድኅን ስሑል ሽረን በቴክኒካል ዳይሬክተርነት የሚመራ ይሆናል። በ 2005 ቡድኑ በብሄራዊ ሊግ መወዳደር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ፕሪምየር ሊግ እስገባበት ዓመት ድረስ ቡድኑን ያገለገለው በረከት ወደ አሰልጣኞች ቡድን የተቀላቀለው ገብረኪሮስ አማረን ቦታ ተክቶ ይሰራል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡