በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ትግራይ ስታድየም ላይ መቐለ 70 እንደርታን ከ ወልዋሎ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በመቐለ 70 በኩል ባለፈው ሳምንት ደደቢትን ካሸነፈው ስብስብ ያሬድ ብርሃኑን በያሬድ ከበደ እንዲሁም ሥዩም ተስፋዬን በቢያድግልኝ ኤልያስ ተክተው ሲገቡ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ካሸነፈው ስብስባቸው አብዱልዓዚዝ ኬይታ እና ብርሃኑ ቦጋለን በበረከት አማረ እና ዳንኤል አድሓኖም ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በእጅግ በርካታ ደጋፊ እና አስደናቂ የሜዳ ድባብ ታጅቦ በጀመረው ጨዋታ ምንም እንኳ በሁለቱም በኩል ተቀዛቅዞ ቢጀምርም ብዙም ሳይቆይ የወልዋሎ የበላይነት የታየበት ነበር። በጨዋታው ለረጅሙ አጥቂ ክሪስቶፈር ችዞባን ኢላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች ለመጫወት አስበው የገቡ የሚመስሉት ቢጫ ለባሾቹ በተለይም በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች የተሻሉ ነበሩ።
እንየው ካሳሁን በረጅሙ ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው በመጀመር በክሪስቶፈር ችዞባ እና አብዱልራሕማን ፉሴይኒ ጥሩ የጎል ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ፕሪንስ አሻምቷት ከጎሉ ጠርዝ ቅርብ ርቀት ተነጥሎ የነበረው ቺዞባ መቷት ሶፈንያስ ሰይፈ በጥሩ ሁኔታ የመለሳት ኳስ ወልዋሎዎች ከፈጠሯቸው ዕድሎች የተሻለች ነበረች። ቢጫ ለባሾቹ ከነዚህ ሙከራዎች ውጭም በ እንየው ካሳሁን አማካኝነት የፈጠሯት ዕድልም ተጠቃሽ ነበረች። በአስራ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይም ብልጫቸውን በጎል የሚያጅቡበትን አጋጣሚ በአግባቡ ተጠቅመወል። እንየው ካሳሁን ከመስመር የተሻገረችለት ኳስ በጥሩ ሁኔታ መትቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።
በመጀመርያው አጋማሽ በተለይም በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በተጋጣሚያቸው ብልጫ የተወሰደባቸው ምዓም አናብስት ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ግን በአንፃራዊነት የተሻለ በመንቀሳቀስ በርካታ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። ዮናስ ገረመው በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከቅጣት ምት ሞክሯት በረከት አማረ በመለሳት ቅጣት ምት ሙከራቸው የጀመሩት መቐለዎች በያሬድ ከበደ እንዲሁም በኦሴይ ማውሊ ሙከራዎች አድርገው ነበር በተለይም ያሬድ ከበደ በራሱ ጥረት ይዞ ገብቶ በመምታት ያደረጋት ሙከራ ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ ካደረጋቸው ሙከራዎች የተሻለች ግብ የቀረበች ነበረች። ቀስ በቀስ ከአጥቂዎቹ ቅርብ ርቀት ሲጫወቱ የታዩትን ሁለቱ አማዮች ከጥልቀት እንዲነሱ በማድረግ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ያደረጉት መቐለዎች ምንም እንኳ የተሻለ ቢንቀሳቀሱም በመስመር አጨዋወቱ የፈጠሯቸው የጠሩ ዕድሎች ግን ጥቂት ነበሩ።
በሰላሳኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማውሊ በራሱ ጥረት ይዞ ገብቶ ያሻገረው ኳስ ከጉዳት የተመለሰው ያሬድ ከበደ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በዚህም ባለፈው ከደደቢት ጋር በነበረው ጨዋታ ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶች ያቀበለው ጋናዊው አጥቂ ኦሴይ ማውሊ በሁለት ጨዋታዎች ለሶስት ግቦች መቆጠር ምክንያት ሆኗል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተሻለ የተንቀሳቀሱት 70 እንደርታዎች በቢያድግልኝ ኤልያስ እና ኦሴይ ማውሊ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በተለይም ሚካኤል ደስታ ከመዓዘን አሻምቷት ቢያድግልኝ ኤልያስ በግንባር ያደረጋትን ሙከራ በረከት አማረ ወጥቶ ባያድናት ምዓም አናብስትን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።
ሁለተኛው አጋማሽ ማራኪ እንቅስቃሴ እና እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች በታዩበት ሲሆን በሁሉም መለከያዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። በዚህ አጋማሽ ተሻሽለው የተመለሱት መቐለዎች ምንም እንኳ በኳስ ቁጥጥር ተሽለው ቢታዩም የፈጠሯቸው የጠሩ የግብ ዕድሎች ጥቂት ነበሩ።
ከነዚህም ሚካኤል ደስታ አሻምቷት ኦሴይ ማውሊ ያደረጋት ሙከራ ፣ ቢያድግልኝ አሻምቷት ኦሴይ ማውሊ በግንባሩ ገጭቶ በረከት አማረ የመለሳት ኳስ ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም በኦሴይ ማውሊ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው የግቡን አግዳሚ ተመልሶባቸዋል ፤ አጥቂው በግሉ ጥረት ይዞ ገብቶ በመምታት ነበር ሙከራውን ያደረገው።
በመጀመርያው አጋማሽ ከነበራቸው ድንቅ አጀማመር ወርደው የታዩት ወልዋሎዎችም ምንም እንኳ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ሙከራዎች ከማድረግ ግን አልቦዘኑም።
በተለይም አጥቂዎቹ የመቐለ ተከላካዮች ትኩረት ማጣት ተጠቅመው ያደረጓቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ልዩ ብቃት ባይመክኑ ኖሮ ቢጫ ለባሾቹ መሪ ለመሆን የተቃረቡበት ዕድል አግኝተው ነበር። ቺዞባ የተከላካዮቹ ስህተት ተጠቅሞ ያደርገው ሙከራ እና ተቀይሮ የገባው አዶንጎ በተመሳሳይ የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። ወልዋሎዎች ከዚህም በተጨማሪ በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ጥሩ መከራ ማድረግ ችለው ነበር።
ውጤቱ በዚህ መጠናቀቁ ተከትሎ መቐለዎች ከተከታዮቻቸው ያላቸው ልዩነት ለማስጠበቅ የነበራቸው ዕድል ሲያመክኑ ከተከታታይ 10 ጨዋታዎች ድል በኋላም ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ጥለዋል። ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ያገኙት ወልዋሎዎች በአንፃሩ ደረጃቸውን ማሻሻላቸውን ቀጥለውበታል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡