ባምላክ ተሰማ ታሪካዊውን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራል

ከአፍሪካ ውጪ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የአፍሪካ ክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ (ሱፐር ካፕ) ዛሬ ምሽት በአረባዊቷ ምድር ኳታር ይከናወናል። ኢትዮጵያዊው ዓለምአቀፍ ዳኛ ባምላክ ተሰማም ጨዋታውን እንዲመራ ተመድቧል።

ከ1993 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጀምሮ መካሄድ የጀመረው የአፍሪካ አሸናፊዎች አሸናፊ ወይም ሱፐር ካፕ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ ውጪ በኳታር መዲና ዶሀ አልታሀኒ ቢን ጃሲን ስታዲየም ይደረጋል፡፡ የ2018 የቻምፒዮንስ ሊግ ባለ ድሉ የቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከኮንፌድሬሽን አሸናፊው የሞሮኮው ራጃ ክለብ አትሌቲክ (ራጃ ካዛብላንካ) ዛሬ ምሽት 1:00 የሚያደርጉ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ረዳቶቹ  ደቡብ አፍሪካዊው ዛኬሎ ቱሲ ሲዌላ እና ሱዳናዊው ዋሌድ አህመድ ዒሊ ጋር በጥምረት ጨዋታውን የሚመሩት ይሆናል፡፡

በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ኤስፔራንስ በሜዳው አልአህሊን 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የመጀመሪያውን የ3-1 ሽንፈት ገልብጦ ቻምፒዮን ሲሆን ባምላክ ተሰማ ጨዋታውን መምራቱ ሲታወስ የ2018 የዓለም ክለቦች ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በቅርብ ጊዜያት የመራቸው ትልልቅ ዓለምአቀፍ ውድድሮች ናቸው።

ዶሃ ላይ የሚካሄው ጨዋታ ላይ ለመታደም የተዘጋጁት ትኬቶች በሙሉ ተሽጠው ማለቃቸው የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ቀደም ዋንጫውን በተመሳሳይ አንድ አንድ ጊዜ ማንሳት የቻሉት ሁለቱ ክለቦች ለሁለተኛ ድላቸው ይፋለማሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *