የ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ የከፍተኛ ሊግ ቀሪ ጨዋታዎች ቅዳሜ መደረግ ሲጀምሩ በምድብ ሐ ጅማ አባ ቡና፤ በምድብ ለ ደግሞ ዲላ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ጅማ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን የጋበዘው ጅማ አባ ቡና 2-1 አሸንፏል። ቀዝቃዛና ሳቢ እንቅስቃሴ ያልታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መሀል ሜዳ ላይ የተገደበ፤ በጉሽሚያዎች የታጀበ በዳኛ ፊሽካ በተደጋጋሚ የሚቆራረጥ አሰልቺ ጨዋታ ነበር። አልፎ አልፎ ወደ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ግብ ክልል በመድረስ ሙከራ ለማድረግ የሚጥሩት ጅማ አባቡናዎች የቢሾፍቱን ተከላካይ መስመር ተደርበው ከሚወጡት ኳሶች ውጭ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን ጅማ አባ ቡናን በውሰት የተቀላቀለው አቤል አምበሴ በ32ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በ35ኛው ደቂቃ በግምት ከ20 ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ዳዊት ሞገስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቮች አቻ ሆነዋል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ሁለቱ ቡድኖች የተሻለ እቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጅማ አባቡና ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቮች ትኩረታቸው ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ሰዓት ማባከንን በተደጋጋሚ ሜዳ ውስጥ አሳይተዋል። ቢሾፍቱዎች የአሰገራሚ ሁኔታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ኳስን ተቆጣጥረው ሲጫወቱ አባ ቡና ላይ ብልጫም ጫናም በመፍጠር የባለሜዳዎቹን ደጋፊዎች ትኩረትና አድናቆት ማግቸትም ችለው የነበረ ቢሆንም ትኩረታቸው ሰዓት ማዘግየት ላይ በማድረጋቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል። በ88ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይሮ የገባው ካሚል ረሺድ ባለሜዳዎቹን አሸናፊ ያደረገች ግብ በማስቆጠር አባ ቡና በሜዳው ሶስት ማግኘት አስችሏል፡፡
በምድብ ለ ሶዶ ስታድየም ላይ በአንደኛው ዙር ደካማ ጉዞ ያደረገው ዲላ ከተማ ባለሜዳው ሶዶ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር በድል ጀምሯል።
ስመኘው ገመዳ የመጀመሪያ ድላቸውን አስመዘገቡ።
የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በመኖሩ ምክንያት ወደ ቅዳሜ የተዘዋወረው ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የዲላ ደጋፊዎች የምስጋና ባነር በመያዝ በጌዲዎ ማህበረሰብ ላይ በደረሰው መፈናቀል ከጎናቸው ለነበሩት በሙሉ ምስጋና አሰተላልፈዋል። በ65ኛው ደቂቃ የመስመር ተጫዋቹ ኤልያስ እንድሪስ ለዲላ የማሸነፊያውን ግብ ሲያስቆጥር በ74ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ሶዶ ተጫዋች ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ፉዓድ አህመድ ቢመታውም የዲላው ግብ ጠባቂ ዳግማዊ መኳንንት ከግብነት ታድጓታል። ጨዋታውም በእንግዳው ቡድን አሸናፊነት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡