ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

የቅድመ ዳሰሳችን ቀጣዩ ትኩረት የድቻ እና የሀዋሳ ጨዋታ ነው።

የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት የሚጫወቱት ድቻ እና ሀዋሳ ነገ 09፡00 ላይ በሶዶ ስታድየም ይገናኛሉ። በገለልተኛ ስታድየም ከሌላው የደቡብ ክለብ ሲዳማ ጋር ነጥብ የተጋራው ወላይታ ድቻ ጥሩ ተስፋ ያሳየበትን ጨዋታ ማድረግ ችሎ ነበር። ሆኖም በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ለሚገኙት የጦና ንቦቹ በፍጥነት ወደ ድል መመለስ እጅግ ወሳኝ ነው። በባዬ ገዛኸኝ እና አላዛር ፋሲካ ጥሩ የአጥቂ ጥምረት የፈጠረው ቡድኑ አማካይ ክፍሉም ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚያመች እየሆነ ነው። ልምድ ያለው ደጉ ደበበን ያካተተው የተከላካይ ክፍሉም በሂደት ከስህተቶች ሊርቅ የሚችልበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ይታመናል። በሌላ በኩል ግን ከነቸርነት ጉግሳ የሚነሳው የቡድኑ የመስመር ጥቃት አቅም ማጣት እና ግልፅ የግብ ዕድሎችን ማባከን ዋጋ ሊያስከፍለው የሚችሉት ችግሮቹ ናቸው። በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት የወጣው በረከት ወልዴ መመለስ ጉዳይ ከማጠራጠሩ በቀር በወላይታ ድቻ በኩል የሚነሳ የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን አዲስ ፈራሚው ኃይሌ እሸቱም በጨዋታው ተሳታፊ የሚሆንበት ዕድል ይኖራል።

በሂደት ከዋንጫ ፉክክሩ በመራቅ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካቱ ወደ መሪዎቹ የመቅረብ ዕድሉን አምክኖበታል። በቀጥተኛ እና ፈጣን የመስመር ጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ መግባትን ምርጫቸው የሚያደርጉት ሀይቆቹ ከሜዳ ውጪ በሚደሩጉ ጨዋታዎች ላይ ደካማ ቁጥር ያላቸው መሆኑ እና በሜዳው ሽንፈት ያላስተናገደ ቡድን መግጠማቸው ዕድላቸውን የሚያጠበው ቢሆንም ወደ ኦሊምፒክ ቡድኑ የላኳቸው ተጫዋቾች መመለስ በነገው ጨዋታ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። በተለይም የመስመር ተመላላሹ ደስታ ዮሀንስ ተሻጋሪ ኳሶች ጥራት እና የእስራኤል እሸቱ ለአየር ላይ ኳሶች የተመቸ መሆን በመሰል ሁኔታዎች ክፍተት ለሚታይበት የወላይታ ድቻ የኋላ መስመር ፈተና መሆናቸው አይቀርም። ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆንም በተመሳሳይ ከብሔራዊ ቡድኑ የተመለሰ ሲሆን ገብረመስቀል ዱባለ በጉዳት ፣ አዲስአለም ተስፋዬ ደግሞ በወልዋሎ ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርዲ እንዲሁም የወረቀት ጉዳይ ያላለቀለት አጥቂው አትራም ኩዋሜም በዚህ ጨዋታ ተካፋይ አይሆኑም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገበት 2006 ወዲህ ሁለቱ ቡድኖች 11 ጊዜ ተገናኝተው ድቻ 5 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ ሀዋሳ ከተማ ሁለት አሸንፏል ፤ በ4 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 12 ሲያስቆጥር ሀዋሳ 8 አስቆጥሯል።

– ሶዶ ላይ ሽንፈት ያላገኘው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሦስቱን በድል አራቱን ደግሞ በአቻ ውጤቶች አጠናቋል።

– ከሜዳው ውጪ አንድ ድል ብቻ ማዝመዝገብ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሦስቴ ሲሸነፍ ሦስቴ ነጥብ መጋራት ችሏል።

ዳኛ
– ሀዋሳ ከተማን በአንድ ጨዋታ ላይ የዳኘው ኃይለየሱስ ባዘዘው በዚህ ጨዋታ ላይ ተመድቧል። ካርድ ባለመምዘዝ የሚታወቀው ኃይለየሱስ በእስካሁኖቹ ስድስት ጨዋታዎች 14 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲያሳይ ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችም ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኄኖክ አርፌጮ

ኃይማኖት ወርቁ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ

ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ –ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሄኖክ ድልቢ– ታፈሰ ሰለሞን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *