ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በሌላኛው የባህር ዳር እና ሲዳማ የ18ኛ ሳምንት መርሀ ግብር  ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች….


በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታድየም ባህር ዳር ከተማ ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 9፡00 ላይ ይጀምራል። ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ሁለተኛውን ዙር የጀመሩት ባህር ዳሮች ሳምንት በሽረ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። 25 ነጥብ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ የሚያገኙት ነጥብ የተለየ የደረጃ መሻሻልን ሊያመጣላቸው ባይችል እንኳን ወደ ነገ ተጋጣሚያቸው ለመቅረብ የሚያግዛቸው ነው። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት በርካታ ተጫዋቾቹን አጥቶ የነበረ መሆኑ ሲታወስ ከእነርሱም መካከል በጉዳት ያልተሰለፉት ኤልያስ አህመድ እና አስናቀ ሞገስ ከጉዳታቸው በማገገማቸው ለነገው ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል። ነገር ግን ቡድኑ የመስመር ተከላካዩን ሣላአምላክ ተገኝን እና የመስመር አጥቂውን ወሰኑ ዓሊን ግልጋሎት በነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት አያገኝም። ከሁለቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ በኦሊምፒክ ቡድኑ ጥሪ ቀርቦላቸው የነበሩት ምንተስኖት አሎ እና ወንድሜነህ ደረጄ ቡድኑን ባለመቀላቀላቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። በመሆኑም ሙሉ ለሙሉም ባይሆን እንኳን አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በብዛት ሲጠቀሙበት የሚታየውን የመጀመሪያ አሰላለፍ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሣለአምላክ አለመኖር ግን የአዲስ ግደይን ከግራ መስመር የሚነሳ ጫና ለመቋቋም አዳጋች ሊያደርግባቸው ይችላል።

የሊጉን መሪ በስምንት ነጥቦች ልዩነት በመከተል ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ከሁለተኛው ዙር መግቢያ በኋላ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ማሳካታቸው ልዩነቱ የዚህን ያህል እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል። ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዘው ካልተመለሱም ደረጃቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ዕድል አለ። በመሆኑም ጨዋታውን በማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚያከናውኑት ይሆናል። በወላይታ ድቻው ጨዋታ በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸው ብልጫ እንዲሁም አብዝተው በመስመር ጥቃት ላይ መመርኮዛቸው ለተገማችንት ሲያጋልጣቸው መታየቱ ደግሞ በሜዳው ጠንካራ በሆነው ተጋጣሚያቸው እንዲፈተኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። በተለይም ባለሜዳዎቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማግኘት ከቻሉ ሲዳማዎች ጫና ውስጥ የሚገቡበት ዕድል የሰፋ ነው። ሆኖም ውጤት ቀያሪው የቡድኑ የመስመር ጥቃት በሀብታሙ ገዛኸኝ ከ ኦሊምፒክ ቡድን መመለስ ይበልጥ እንደሚጠናከር ይገመታል። በሌላ በኩል ዮናታን ፍሰሀ ጉዳት ላይ የነበሩት አበባየው ዮሀንሰና እና ጫላ ተሺታን ዝርዝር በመቀላቀሉ ጨዋታው ያልፈዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በመጀመሪያው ዙር ሁለቱን ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶች የተሰጡበት ሲሆን ሁለቱ ወደ ግብነት ተቀይረው ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

– በሜዳቸው በመጠንካራ አቋማቸው የቀጠሉት የጣና ሞገደቹ ምንም ሽንፈት ያልገጠማቸው ሲሆን አራት የድል እና አራት የአቻ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። 

– ሲዳማ ቡና ከድቻ ጋር በገለልተኛ ማዳ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ሳይጨምር ከሜዳው ውጪ ስድስት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ድል የቀናው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በተረፈ ሦስቴ ነጥብ ሲጋራ ሁለት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።
 
ዳኛ

– ሲዳማ ከፋሲል ፤ ባህርዳር ደግሞ ከወልዋሎ የተገናኙባቸውን ጨምሮ ሰባት ጨዋታዎችን የዳኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ይህን ጨዋታ ይመራዋል። አርቢትሩ 25 የቢጫ ካርዶችን መዞ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ተስፋሁን ሸጋው – አሌክስ አሙዙ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ

ፍቃዱ ወርቁ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

መሳይ አያኖ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ሰንደይ ሙቱኩ – ሚሊዮን ሰለሞን

ወንድሜነህ ዓይናለም – ዮሴፍ ዮሃንስ – ግርማ በቀለ

ሀብታሙ ገዛኸኝ – መሀመድ ናስር –  አዲስ ግደይ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *