ባህር ዳር ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዳደገ ካስፈረማቸው ስምንት ተጨዋቾች ሁለቱን ከክለቡ ለመቀነስ ወስኗል። በዚህም ከወላይታ ድቻ ቡድኑን የተቀላቀለው ታዲዮስ ወልዴ እና አህመድ ቢን ዋታራ በድርድር ክለቡን እንዲለቁ እንደተደረጉ ለማወቅ ተችሏል።
ከወላይታ ድቻ በፊት በአርባ ምንጭ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ የተጫወተው ታዲዮስ እንደታሰበው ቡድኑን ሳያገለግል ዓመቱን በጉዳት እና በአቋም መውረድ በማሳለፍ በቋሚነት ለመሰለፍ ሲቸገር ታይቷል። ከታዲዮስ በተጨማሪ ቡድኑን በድርድር የለቀቀው አህመድ ቢን ዋታራ በክረምቱ የጣናው ሞገዶቹን ከተቀላቀሉ አራት የውጪ ዜግነት ካላቸው ተጨዋቾች አንዱ ነበር። ተጨዋቹ በተለይ የቡድኑ ዋና አጥቂ ጃኮ አራፋት እንዲሁም ፍቃዱ ወርቁ በጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀይረው ሲወጡ እንደ ሁለተኛ አማራጭ እየገባ የቡድኑን የፊት መስመር ሲመራ ቆይቷል። ይሁንና እነዚህ ሁለት ተጨዋቾች እንደታሰበው አሰልጣኙን ማሳመን ስላልቻሉ ከቡድኑ ሙሉ ለሙሉ እንደተለያዩ ታውቋል።
ሁለቱን ተጨዋቾች ያሰናበተው ባህር ዳር ከተማ በጥቂት ቀናት ውስጥ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ ሊቀላቅል እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡