ሪፖርት | የዜናው ፈረደ ማራኪ ጎል ለባህርዳር ከተማ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስገኘች

ጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከማራኪ ጎል ጋር ያስመለከተን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባህርዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል ተካሂዶ የጣና ሞገዶቹ 1-0 አሸንፈዋል።

ባለሜዳዎቹ ባህርዳሮች በ17ኛው ሳምንት በሱሑል ሽረ አንድ ለዜሮ ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ የሆኑት ሳላምላክ ተገኝ እና ወሰኑ ዓሊን በማሳረፍ በማራኪ ወርቁ እና አስናቀ ሞገስ እንዲሁም ጃኮ አረፋትን በዜናው ፈረደ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር አንድ አቻ ነጥብ ከተጋራው ቡድናቸው ዮናታን ፍስሃ ፣ ሚሊዮን ሰለሞን ፣ ወንድሜነህ ዓይናለም እና አዲሱ ተስፋዬን በማስወጣት ግሩም አሰፋ ፣ ትርታዬ ደመቀ ፣ ዳዊት ተፈራ እና ሐብታሙ ገዛኸኝን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

እጃቸው ላይ ባጋጠመ ጉዳት ከእነህመማቸው ቡድኑን የመሩት የአሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታችው ባልተለመደ ሁኔታ ማራኪ ወርቁን የቀኝ መስመር ተከላካይ፤ ዜናው ፈረደንም እንዲሁ የፊት አጥቂ አድርገው የተጠቀሙ ሲሆን ባህርዳሮች በተደጋጋሚ ወደ ፊት በመሄድ ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ለጎል የቀረበ ሙከራ ግን መመልከት የቻልነው 7ኛው ደቂቃ ነው። አማካዩ ዳንኤል ኃይሉ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ጀምሮ ከግራ መስመር ኳሱን እየገፋ በመሄድ በሲዳማ የሜዳ ክፍል በመግባት ከፍቃዱ ወርቁ በጥሩ ሁኔታ ነፃ ኳስ ግርማ ዲሳሳ ቢቀበልም ራሱ ኳሱን ይጠቀምበታል ሲባል መልሶ ለፍቃዱ ለመስጠት ሲሞክር የተበላሸው ኳስ ለጎል የቀረበ እድል ነበር።

በሲዳማ በኩል በራሳቸው ሜዳ ክፍል አብዝተው ኳሱን በመቀባበል ላይ ያመዘኑ ሲሆን በአንድ አጋጣሚ 10ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ተስፋዬ በባህርዳር ተከላካዮች መሐል አሾልኮ ያቀበለውን አዲስ ግደይ ቆርጦ በመግባት ከርቀት የመታውን ጠንካራ ኳስ ግብ ጠባቂው ሐሪሰን ሔሱ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣው አስደንጋጭ ሙከራ ነበር። ምልልስ በበዛበት በዚህ ጨዋታ ብዙም ሳይቆይ ዳንኤል ኃይሉ ከማዕዘን ምት አቅራቢያ ያሻገረውን ፍቃዱ ወርቁ አምሰት ከሃምሳ ውስጥ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ተወርውሮ የመታው መረቡ ላይ አረፈ ሲባል ለጥቂት አንግሉን ታኮ ሊወጣበት ችሏል።

እጅግ ማራኪ በሆነ ቅብብሎች ወደ ጎል የሚደርሱት ሁለቱም ቡድኖች ጎል አያስቆጥሩ እንጂ በእንቅስቃሴ ረገድ የሚያደርጉት ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግር ተመልካቹን እጅግ ያዝናና ነበር። ያም ቢሆን መጨረሻው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ባለመረጋጋት እና ከውሳኔ ችግር የተነሳ የሚባክኑ ኳሶችን በተደጋጋሚ ለመመልከት ችለናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከባህርዳር በኩል ግርማ ዲሳሳ እና ፍቃዱ ወርቁ በእንግዶቹ በኩል አዲስ ግደይ እና ዳዊት ተፈራ ኢላማውን ባይጠብቁም የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ከእረፍት መልስ የጨዋታውን ልዩነት የፈጠረ አጋጣሚ ሳይታሰብ 47ኛው ደቂቃ ላይ ተፈጥሮ ለጎሉ መቆጠር ምክንያት ሆኗል። የቡድኑን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አማካዩ ደረጄ መንግስቱ የጣለለትን ኳስ ዜናው ፈረደ አየር ላይ እያለ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥሮ በሲዳማ ቡና ተከላካይ ጭንቅላት ላይ አሻግሮ በማለፍ እዛው አየር ላይ እያለ በመምታት ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ መረብ ላይ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የጣና ሞገዶችን መሪ ማድረግ ቻለ።

ከደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ የመስመር ተከላካይ በመሆን ባልተለመደ ሁኔታ አዲስ ግደይን የመቆጣጥር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የዋለው ማራኪ ወርቁ ከመስመር ወደ መሐል ሜዳ ኳሱን በፍጥነት ተከላካዮችን በማለፍ ሲዳማ ሳጥን ውስጥ ገብቶ አገባው ሲባል ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል እንደምንም ተንሸራቶ ያወጣበት አጋጣሚ ጎል መሆን የሚችል ነበር።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በፍጥነት ወደ ጨዋታው ለመግባት መሐመድ ናስርን በአዲስ ተስፋዬ፣ ግሩም አሰፋን በወንድሜነህ ዓይናለም በመቀየር ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተጭነው ቢጫወቱም ግልፅ የግብ ዕድል ለመፍጠር ይዘገዩ እንደነበረ ለማየት ችለናል። 60ኛው ደቂቃ ከባህርዳር ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ወንድሜነህ ዓይናለም አምስት ከሃምሳ ውስጥ ቢያገኘውም በግቡ አናት ሲሰዳት 65ኛው ደቂቃ ላይ ሐብታሙ ገዛኸኝ ሳይታሰብ ከርቀት የባህርዳሩ ግብ ጠባቂ ሐሪሰን ከግብ ክልሉ መውጣት አይቶ በተዘናጋበት ሁኔታ በመምታት ለጥቂት በግቡ አግዳሚን ታኮ ሊወጣበት ችሏል። በስታዲየሙ የነበረው ተመልካችም በዚህች ሙከራ ተደናግጦ በዝምታ ሲዋጥ አስተውለናል። ሲዳማዎች ተጭነው እየተጫወቱ ባለበት ቅፅበት ሁለተኛ ጎል መሆን የሚችል እድል ባህርዳሮች በመልሶ ማጥቃት ከሲዳማ በተሻለ ክፍት ሜዳ አግኝተው አጥቂያቸው ግርማ ዲሳሳ የሚያመክናቸው የግብ ዕድሎች ያስቆጩ ነበር።

የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በርካታ እጅግ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች የተመለከትንበት ሲሆን በእንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች በኩል ወንድሜነህ እና አዲስ ግደይ ተቀባብለው አዲስ ወደ ጎል መቶት ሐሪሰን ያዳነበት፤ 81ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አዲስ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር አምስት ከሃምሳ ውስጥ መሬት ለመሬት አቀብሎት አዲስ ግደይ በቄንጥ ተረከዝ መቶት ለጥቂት የወጡት ኳሶች ጎል መሆን የሚችሉ ነበሩ። በአንፃሩ ባህርዳሮች ተቀይሮ በገባው አጥቂ ጃኮ አረፋት አማካኝነት ሁለት ጊዜ ነፃ ግልፅ የሆኑ የጎል አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት በመቅረት ጨዋታው በባለ ሜዳዎቹ ባህር ዳሮች 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *