ባህር ዳር ላይ ከተደረገው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች በዚህ መልኩ አስተያየት ሰጥተዋል።
“ዘጠና ደቂቃ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለናል” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ
ስለጨዋታው
ቡድኔን እንደተመለከታችሁት ከዚህ በፊትም እንደምናገረው ሁሉም ተጫዋች በየትኛውም ቦታ ቢሰጠውም ማገልገል አለበት። ማራኪ ወርቁ ዛሬ የተጫወተበት ቦታ እና ከማን ጋር እንደተጫወተ አይታችሁታል። በ.ከሊጉ ምርጥ የመስመር አጥቂ አዲስ ግደይ ጋር ነው። ስለዚህ ሁሉም ተጫዋች ልበ-ሙሉ መሆን ያስፈልጋል። ዘጠና ደቂቃ በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ ችለናል።
የሜዳውን ውጤት ከሜዳ ውጪ አለመድገሙ
ከሜዳ ውጪ ቡድኔ ሲወጣ ብዙ የሚያጋጥሙን ነገሮች አሉ። በዛ ላይ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በጉዳት እና ሌላም ምክንያት ከቡድኑ ጋር የሉም። ያም ቢሆን ቡድኔ እስካሁን እያስመዘገበ ያለው ውጤት በጣም አስገራሚ ነው። ከክለብ አመራሮቼ ጋር ተነጋግሬ ከሜዳ ውጭ ስንጫወት በትክክል የሚዳኙ ዳኞች እንዲመደቡልን ማድረግ አለብን።
የዜናው ፈረደ የአጥቂነት ሚና
እኔ ነግሬያችኋለው። ተጫዋች የሚገባበት እና የሚወጣበት ጊዜ አለው። ዛሬ ማራኪን በዚህ ቦታ ይጫወታል ብሎ የጠበቀ የለም። ስለዚህ እኔ በሚመስለኝ የራሴን ፍልስፍና ነው የምተገብረው። ከዚህ በፊትም ውጤታማ ነኝ፤ አሁንም ውጤታማ ነኝ። ባህርዳር ወደፊት ይሄዳል። ሰኔ ላይ የምናየው ይሆናል።
“ሽንፈት አይደለም አቻ እንኳን ለዛሬው አጨዋወታችን አይመጥነንም” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
የጨዋታው እንቅስቃሴ
ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፤ ጥሩ ነገሮችን መመልከት ችለናል። በጨዋታውም ብልጫ ወስደን መጫወት ችለናል። በዛሬው ጨዋታ የተረዳሁት በልጠህም መሸነፍ እንዳለ ነው። ፍፁም ዘጠና ደቂቃ ኳሱን ተቆጣጥረን ተጫውተናል። የጎል ዕድሎችን መጠቀም አልቻልንም። እኛ በሰራነው ስህተት ጎል ተቆጠረብን እንጂ ቡድኔ የሚገርም ነበር። ሽንፈት አይደለም አቻ እንኳን ለዛሬው አጨዋወታችን አይመጥነንም።
ከመሪዎቹ እየራቀ መሆኑ
ሶስተኛ ተከታታይ ከሜዳ ውጪ ጨዋታችን ነው። ያው ከሜዳ ውጪ ስትጫወት ብዙ ነገር አለ። የደጋፊ ጫና፤ የዳኝነት ተፅእኖ አለ። እነዚህን ችለህ ነው የምትጫወተው። በዚህ ሂደት ውስጥ አንድ ለዜሮ ስትሸነፍ ቡድንህ ጥሩ ቢሆን ነው። በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን። ወደ መሪዎቹም እንጠጋለን፤ ብዙም የራቀ ቡድን የለም።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡