ከፍተኛ ትኩረት ካገኙ የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በባለሜዳው ጅማ አባ ጅፋር አሸናፊነት ተጠናቋል።
ጅማ አባጅፋር በአስራ ሰባተኛ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ጦሩ ላይ ጣፋጭ የ4-0 ድልን አስመዝግቦ ከተመለሰው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደረግ የዛሬውን ጨዋታ ሲጀምሩ የአምናው የፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ኦኪኪ አፎላቢ ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ጨዋታ አድርጓል። በቅዱስ ጊዩርጊስ በኩል በሜዳው አዳማ ከተማን አስተናግዶ ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ሶስት ለውጦችን በማድረግ በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድን ተጠርቶ የነበረው ፓትሪክ ማታሲ ለዓለም ብርሃኑን እንዲሁም አቡበክር ሳኒ አብዱልከሪም መሐመድን በመተካት በአዳማው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት የገጠመው ጌታነህ ከበደን ደግሞ አቤል ያለው ተክቶት የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል፡፡
በዋና ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴና ረዳቶቻቸው በጥሩ ብቃት መርተው ያጠናቀቁት የዛሬ ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች በባለሜዳዎቹ ጅማ አባጅፋሮች የጨዋታ የበላይነት ወስደው ሲጫወቱ በመሐል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ እና በሁለቱ መስመሮች በኩል ወደ ጊዮርጊስ ግብ ክልል በመድረስ ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። ማማዱ ሲዴቤ እና ዲዲዬ ለብሪ ወደ መስመሮች በማስፍት ክፍተቶችን ለመፍጠር የሚደርጉት እቅስቃሴም በመጀመርያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ለጊዮርጊስ ተከላካዮች ፈታኝ ሆኖባቸው ነበር። በዚሁ አጋጣሚ በጥሩ የኳስ ቅብብል ዐወት ገብረሚካኤል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የጊዮርጊስ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ አቋቋም ላይ የነበረው አሰቻለው ግርማን ሲጠብቁ በመዘናጋታቸው በፍጥነት ከመሀል የወጣው ማማዱ ሲድቤ ከግራ ወደ መሀል ኳስን እየገፍ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጅማዎችን መሪ ማድረግ የቻለች ግብ አስቆጥሯል።
ጊዮርጊሶች ወደ ጠዋታው ቅኝት የገቡት ከሃያኛው ደቂቃ በኋላ ነበር። በቀኝ መስመር በሄኖክ አዱኛ በኩል የሚያደርጉት የማጥቃት ሽግግር መጨረሻው ውጤታማ ባይሆንም፤ ከቆሙ ኳሶች በሐምፍሬ ሜዬኖ በኩል የሚሻገሩት ኳሶች ተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የሚፈጥሯቸው አጋጣሚዎች በጅማ ተከላካዮች ሲመለሱ የተቀሩት ደግሞ ኢላማቸው ያልጠበቁ ነበሩ፡፡ በእንቅስቃሴ ረገድ ፈረሰኞቹ በረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ የጅማ ተከላካዮችን በይበልጥ ወደ ኃላ እንዲጠጉ ስላደረጋቸው ፈረሰኞቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የነበረባቸውን ጫና በዚህ መልኩ መቀነስ ቢችሉም ተሻጋሪ ኳሶቹ ግን የጠራ የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ውጤታማ አልነበሩም። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ሁለቱ ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ጥሩ እቅስቃሴ በማድረግ የመሸናነፍ ፉክክር ማድረግ ችለዋል። ነገር ግን ወደ ግብ በመድረስና እድሎችን በመፍጠር ረገድ ባለሜዳዎቹ የተሻሉ ነበሩ። ከእረፍት በተመለሱ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጀምሮ በማማዱ ሲድቤ የጠሩ የግብ እድሎችን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በተጨማሪም መስዑድ መሐመድ ሳጥን ውስጥ ተከላካዮችን አታሎ የሞከረውን ፓትሪክ ማታሲ ከወደቀበት ተነስቶ ያዳነው ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማዎች በኩል የተፈጠሩ የጠሩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
የፈረሰኞቹ እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ከተሻጋሪ ኳሶች እድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጓቸው ሙከራዎች ፍሬ ከማፍራት ይልቅ የአባ ጅፋር ተከላካዮች እና የግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ ሲሳይ ሆነዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የዛሬውን ውጤት ተከትሎ በሁለተኛው ዙር ከሶስት ጨዋታ 7 ነጥበ በመሰብሰብ ግብ ያላስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር ደረጃውን በማሻሻል በባህርዳር በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ላይ ሲቀመጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪው ጋር የነበረውን ልዩነት የሚያጠብበት እድል መጠቀም ሳይችል ወደ አራተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡