ኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ ተጉዞ ወልዋሎን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ!
“እኔ ሰራተኛ ነኝ፤ አሰሪ ደግሞ የፈለገውን ያደርጋል። ይሄን መብት አከብራለው” ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው
ጫና ውስጥ ሆነን ነው ጨዋታዎችን እያደረግን ያለነው። ይህንን መሰረት አድርገን ጨዋታው ለኛ ወሳኝ እና በጣም የምንፈልገው ስለነበር ለማሸነፍ አቅደን ነበር የገባነው። ጨዋታው ጥሩ ነው፤ አሸንፈናል።
በሁለተኛው አጋማሽ ስላደረጋቸው ለውጦች
መጀመርያው አጋማሽ እነሱ ጫና ፈጥረው ነበር። እኛ ደግሞ ባልተረጋጋ ስሜት ውስጥ ነበርን። እሱን ለማረጋጋት አንድ የአጥቂ ክፍል ተጫዋች ከጥልቀት እየተነሳ እንዲጫወት አድርገን እሱም ተሳክቶልናል።
ቡድኑ ተከታታይ መሸነፉ በዛሬው ጨዋታ የነበረው ተፅዕኖ
አዎ ጫና ነበረው፤ እሱም ብቻ ሳይሆን ብዙ ተጫዋቾች በብሄራዊ ቡድን ጥሪ እና ጉዳት ምክንያት ከኛ ጋር አልነበሩም። እሱም ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው።
ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ በተደጋጋሚ ስለተጠቀማቸው ረጃጅም ኳሶች
ከሜዳ ውጪ ጨዋታ እንደመሆኑ እና እንደ ነበረብን ጫና ይሄንን ነገር ለማድረግ ገና ጅምር ላይ ነን። በሂደት በቀጣይ ተመልሰው ይመጣሉ።
በሁለተኛው አጋማሽ የታዩት ነገሮች አሉ። ለሱ የሚመቹ ተጫዋቾችም አሉን እና አጨዋወታችን ተመልሶ ይመጣል።
በቀጣይ ከቡድኑ ጋር ስለ መቀጠሉ
እኔ ሰራተኛ ነኝ፤ አሰሪ ደሞ የፈለገውን ያደርጋል። ይሄን መብት አከብራለው። ቀጣይ የሚሆነውን መጠበቅ ነው።
“ዛሬ ጎሎች አልገቡም እንጂ ሌላው ነገር ጥሩ ነው” ዮሐንስ ሳህሌ – ወልዋሎ
ስለ ጨዋታው
በመጫወት በማጥቃት እና በፍላጎት የተሻልን ነበርን።
ቡድኑ አጨራረስ ላይ ስላለው ክፍተት
እንደዚህ በአጭር ግዜ የሚስተካከሉ ነገሮች አይደሉም። እንደዛ ቢሆንማ ኳስ ጨዋታ ቀላል ይሆን ነበር። መሄድ እንችላለን፤ ማጥቃት እንችላለን፤ ማስጨነቅም እንችላለን። መጨረስ ላይ ችግር አለብን። እሱም ዛሬ ዋጋ አስከፍሎናል። እንደ መጀመርያው አጋማሽ ባንጫወትም ጨዋታው ላይ ግን ብዙ ቅጣት ምቶች እና ማዕዝኖች አግኝተን ማግባት አልቻልንም። በጨዋታ ደረጃ የተሻልን እና የሚያረካ ነው። ቡድኑ በየግዜው እየተሻሻለ ነው፤ ነጥቡን ግን ይዘን አልሄድንም። ከነጥቡ ውጭ በሌሎች መለክያዎች ጥሩ ነበርን። ሰዓቱን ባለመግደል ወደፊትም በመሄድ ሙከራ በማድረግም የተሻልን ነበርን። አጨራረስ ላይ ያለውን ችግር ፈትተን እንመለሳለን።
ቡድኑ ሁነኛ የአጥቂ መስመር ተጫዋች አለው ?
ጎል ማግባት የአንድ ሰው ስራ አደለም። ብዙ ቅጣት ምቶች ነው ያገኘነው። እነሱን እንኳ መጠቀም አልቻልንም። ዛሬ እንዳጋጣሚ ጎሎች አልገቡም እንጂ ሌላው ነገር ጥሩ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡