ሪፖርት | ፋሲል የመቐለን ተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዞ በመግታት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል

ጎንደር ላይ የተደረገው የፋሲል ከነማ እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ በዓለምብርሀን ይግዛው ብቸኛ ጎል በአፄዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ በዛብህ መለዮ እና ሰዒድ ሁሴንን በማሳረፍ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሀብታሙ ተከስተን በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲያካትት በትግራይ ደርቢ ነጥብ የተጋረው መቐለ 70 እንደርታ ደግሞ በሶፎንያስ ሰይፈ ፣ ያሬድ ሀሰን እና ዮናስ ገረመው ቦታ ፍሊፕ ኦቮኖ ፣ አንተነህ ገብረክርስቶስ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ተጠቅሟል።

በጨዋታው አቶ ኢሳያስ ጅራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ አበበ ገላጋይ የማርኬቲንግ ክፍል ሰብሳቢ እንዲሁም የሁለቱ ክለቦች ስራ አስኪያጆች ጨዋታውን ለመከታተል ከጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አዳነ ጋር በመሆን ስታድየም ተገኝተዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት አፄዎቹ በሁለተኛው ደቂቃ ባገኙት የማዕዘን ምት የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አስመልክተዋል። በዚህም ደቂቃ ሰለሞን ሐብቴ ያሻገረውን የማዕዘን ምት ኢዙ አዙካ በግምባሩ ሞክሮ ቡድኑን ገና በጊዜ መሪ ለማድረግ ጥሮ ወደ ውጪ ወቶበታል። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አስበው የገቡ የሚመስሉት መቐለዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ባገኙት ዕድል የፋሲሎችን የግብ ክልል ለመፈተሽ ጥረት አድርገዋል። በቅብብል ስህተት አማካኝነት ያገኙትን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከፋሲል የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ጋር ታግሎ ለማውሊ አሰይ አቀብሎት ማውሊ አምክኖታል። ከእነዚህ ሁለት ሙከራዎች በኋላ የተረጋጋ እንቅስቃሴ ያላስመለከቱን ሁለቱ ቡድኖች ጥርት ያሉ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ የሚመስሉት አፄዎቹ በ10ኛው ደቂቃ ጥሩ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህ ደቂቃ በሚገርም ሽግግር (ከመከላከል ወደ ማጥቃት) ወደ መቐሌዎች የግብ ክልል የደረሱት ፋሲሎች ከቀኝ መስመር ሰለሞን ያሻገረውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ ሞክሮት አሌክስ ተሰማ እንደምንም በማውጣት ኳሷን ከግብነት ታድጓታል።

በመስመር ላይ አጨዋወት ጨዋታውን የቀጠሉት ፋሲሎች አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መቐሌዎች ሜዳ ላይ አሳልፈው ቢንቀሳቀሱም ጥሩ ጥሩ እድሎችን ሰብረው እየገቡ ለመሞከረ ሲቸገሩ ታይቷል። ጥብቁን የመቐሌ የመከላከል አደረጃጀት ሰብረው መግባት ያልቻሉት የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጨዋቾች የግብ ማግባት አማራጫቸውን ከቆሙ እና ከመስመር በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ተንቀሳቅሰዋል። በ16ኛው ደቂቃም ኢዙ አዙካ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የቅጣት ምት ያገኙት ፋሲሎች በሱራፌል ዳኛቸው አማካኝነት አጋጣሚውን ወደ ግብ ሞክረው ለጥቂት ወጥቶባቸዋል። በ29ኛው ደቂቃም በቀጥተኛ አጨዋወት ግብ ለማስቆጠር የጣሩት አፄዎቹ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኦቮኖ በቀላሉ አድኖበታል። የመሀል ሜዳው ብልጫ ሙሉ ለሙሉ ከእጃቸው ያመለጣቸው ተጋባዦቹ መቐለዎች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ማዊሊ አሴይን የመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች ላይ ከተሰለፈበት የፊት መስመር ወደ መሃል በመሳብ የተወሰደባቸውን የመሃልዊ ብልጫ ለመረከብ እና ይበልጥ ለፋሲል የማጥቃት እንቅስቃሴ አስቸጋሪ ለመሆን በመሞከር ተንቀሳቅሰዋል። በጨዋታው ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩት ባለሜዳዎች አሁንም የቆመ ኳስ በመጠቀም በ43ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ሞክረው ከሽፎባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳያስተናግድ ተገባዶ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር መጠነኛ መነቃቃት ታይቶባቸው ወደ ባለሜዳዎቹ ሜዳ ጠጋ ብለው ጨዋታውን የጀመሩት መቐለዎች ብዙም ሳይገፉበት ኳሱን ለፋሲሎች በመተው ወደ መከላከሉ አመዝናዋል። በመሆኑም አፄዎቹ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩ ሲሆን የማዕዘን ምቶችንም አግኝተዋል። በተለይም 52ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኢዙ አዙካ በግንባሩ ገጭቶት አሌክስ ተሰማ ነበር ከመስመር ላይ ያወጣው። አፄዎቹ ከዚህም በኋላም የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ቢቀጥሉም ተጋጣሚያቸውን በቅብብሎች አስከፍተው መግባት ባለመቻላቸው ከመስመር በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች ላይ ለመመርኮዝ ተገደዋል። ሽመክት ጉግሳ በተለፈበት የቀኝ መስመር የሚነሱ የበድኑ ጥቃቶችም በርከት ብለው ይታዩ ነበር።

የባለሜዳዎቹ ተደጋጋሚ የማጥቃት ጥረቶች በተበራከቱባቸው ደቂቃዎች በጫና ውስጥ የገቡት መቐለዎችን ይበልጥ የሚያጋልጥ ክስተት ገጥሟቸዋል። በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ የቢጫ ካርድ ተመልክቶ የነበረው ኦሰይ ማወሊ በ63ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ላይ በሰራው ጥፋት ለሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተዳርጎ ከሜዳ ወጥቷል። በሁኔታው ይበልጥ ለማጥቃት በር የተከፈተላቸው ፋሲሎች ባደረጉት ጥረት አንድ ደቂቃ ቀደም ብሎ ሰለሞን ሀብቴን በመቀየር ወደ ሜዳ የገባው ዓለምብርሀን ይግዛው 65ኛው ደቂቃ ላይ ያሻማው ኳስ በኤፍሬም ኃይሉ በግንባር ተገጭቶ ለጥቂት ነበር የወጣው። በመቐለዎች በኩልም 67ኛው ደቂቃ ላይ ህሀይደር ሸረፋ ከሳጥን ውስጥ ያገኘው ኳስ አክርሮ መቶት ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ በመልካም ሙከራነት የሚነሳ ነበር።

ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ መላካቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች ጥረታቸው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሰምሯል። አምሳሉ ጥላሁን ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ዓለምብርሀን ከጨረፈው በኋላ ኢዙ አዙካ መልሶ ሲነካለት ከሳጥን ውስጥ በመምታት የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል። በቀሩት ደቂቃዎች የፊት አጥቂያቸው ሙጂብ ቃሲምን በመመለስ የተከላካዮቻቸውን ቁጥር ወደ አራት ከፍ ያደረጉት ፋሲሎች ጫና ውስጥ ሳይገቡ ኳስን በማንሸራሸር ለተጋጣሚያቸው የግብ ዕድልን ሳይፈጥሩ እስከመጨረሻው ዘልቀዋል። ይልቁንም ወደ መጨረሻ ላይ ከማዕዘን በተነሱ ኳሶች በኢዙ አዙካ እና ሙጂብ ቃሲም አማካይነት ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። እንግዶቹ መቐለዎች ግን የአቻነት ግብ ፍለጋ ራሳቸውን ወደ ማጥቃት መንፈስ ውስጥ ከማስገባታቸው በፊት ጨዋታው ተጠናቋል።

በውጤቱን አፄዎቹ የመቐለን የ13 ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዞ በመግታት የቻሉ ሲሄን በመካከላቸው የነበረውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ዝቅ በማድረግ ወደ ሁለተኛነት ከፍ ሲሉ መቐለዎች ሽንፈት ከገጠማቸው ሌሎች ተፎካካሪዎቻቸው ያላቸውን ልዩነት ማስፋት ሳይችሉ ቀርተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *