የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም 10:00 ከመጫወቱ አስቀድሞ ዛሬ ጠዋት የመጨረሻ ልምምዱ ሰርቷል።
የመጨረሻ 25 ተጫዋቾቿን ለይታ የመረጠችው አሰልጣኝ ሠላም ዘራይ በትናትናው ዕለት በቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠች ሲሆን ዛሬ ቡድኑ ከ03:00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቶ አጠናቋል። ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት መሆናቸው ሲረጋገጥ በዛሬው ልምምዳቸው ወቅት በነገው ጨዋታ ላይ የመጀመርያ አስራ አንድ ተመራጭ ተጫዋቾን መለየት በሚያስችል መልኩ ለሁለት ተከፍለው ግማሽ ሜዳ ሲጫወቱ ተመልክተናል።
የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ማምሻውን በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዱን የሚሰራ ይሆናል። የጨዋታው ዳኞች አራቱም ከግብፅ ሲሆኑ ኮሚሽነር ኬንያ ናቸው።
ነገ 10:00 በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሚካሄደው የመጀመርያ የማጣሪያ ጨዋታ የተመልካች ሙሉ ገቢ ለሞገስ ታደሰ ህክምና ድጋፍ እንዲውል የተደረገ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ከሦስት ቀን በኋላ በዮጋንዳ ካፓላ የሚያደርጉ ይሆናል።
እንስቶቹ በደርሶ መልስ ጨዋታ ድል የሚቀናቸው ከሆነ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ካሜሩን ትሆናለቸ።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡