ሪፖርት | የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን ዩጋንዳን 3-2 አሸንፏል

ቶኪዮ በ2020 ለምታስተናግደው የኦሎምፒክ ውድድር ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ የጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ዩጋንዳን አስተናግዶ 3ለ2 አሸንፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ወስደው የተንቀሳቀሱት የአሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ተጨዋቾች ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በነበሩት የመጀመሪያ ደቂቃዎችም ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጎል ለማስቆጠር ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በዚህም በአንደኛው እና በስድስተኛው ደቂቃ በተሞከሩ የሴናፍ ዋቁማ እና የሰናይት ቦጋለ ጥብቅ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ከርቀት የተሰጣትን ኳስ ለሎዛ አበራ አመቻችታላት ሎዛ አምክነዋለች። ብልጫቸውን በጎል ማሳመር የፈለጉ የሚመስሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን ተጨዋቾች በ9ኛው ደቂቃ በተገኘ የቅጣት ምትም ሌላ አጋጣሚ ፈጥረው የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። ሙሉ ለሙሉ የበላይነት የተወሰደባቸው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በ11ኛው ደቂቃ ባገኙት የመልስ ውርወራ አማካኝነት በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ደርሰው ነበር። በዚህ ደቂቃ ናቡዬትሜ ሳንድራ ለማቱዞ ሊላም አቀብላት ማቱዞ ሊላም አምክነዋለች።

በ4-3-3 የጨዋታ ፎርሜሽን ጨዋታቸውን እያደረጉ የነበሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሲሰነዝሩዋቸው የነበሩትን የጎል ሙከራዎች በ13ኛው ደቂቃ በግብ አጅበዋል። ቡድኑን በፊት መስመር አጥቂነት ስትመራ የነበረችው ሎዛ አበራ ከግራ መስመር ለማቀበል ብላ የመታችውን ኳስ የተከላካይ መስመር ተጨዋቿ ናሙኪሳ አይሻ በራሷ ግብ ላይ በማስቆጠር የሰላም ተጨዋቾች መሪ ሆነዋል። አሁንም አንዱ ግብ ያላረካቸው የኢትዮጵያ ተጨዋቾች በቀላሉ ወደ ዩጋንዳዎች የግብ ክልል እየደረሱ የግብ እድሎችን ፈጥረዋል። በ24ኛው ደቂቃ ሴናፍ ለሎዛ አቀብላ ሎዛ ባመከነችው እንዲሁም በ28ኛው ደቂቃ የቡድኑ አምበል ብርቱካን በተመሳሳይ ለሎዛ አመቻችታላት ሎዛ ባልተጠቀመችበት ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበረ። በርካታ የግብ እድሎችን በተደጋጋሚ ስታመክን የነበረችው ሎዛ አበራ ከሁለቱ አጋጣሚዎች በተጨማሪ ሌላ ግልፅ አጋጣሚ በ32ኛው ደቂቃ አምክናለች።

በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የተጫወቱት ተጋባዦቹ ከሚያገኟቸው አንዳንድ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ውጪ ወደ ኢትዮጵያዎች የግብ ክልል ሲደርሱ አልታዩም። ነገር ግን ኑቡምባ ፊዮና በ39ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቄሎን አቋቋም ተመልክታ ከመሃል ሜዳ በመታቸው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከዚህች ሙከራ በኋላ የልብ ልብ የተሰማቸው ዩጋንዳዎች በመጨረሻዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በአንፃራዊነት ተሽለው ተንቀሳቅሰዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃም የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ናቡዬትሜ ሳንድራ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድን አንድ ለዜሮ መሪነት ተጠናቋል።

በንፅፅር ከእረፍት መልስ ተጠናክረው የመጡት ዩጋንዳዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በተቃራኒው ተቀዛቅዘው የገቡት የአሰልጣኝ ሠላም ተጨዋቾች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ግብ ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በ57ኛው ደቂቃ ሎዛ ወደ መስመር ወታ ያሻማችውን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ሰርካዲስ አግኝታው በመታቸው ኳስ የሁለተኛ አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት ተጨዋቾቹ አሁንም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ሁለት ወሳኝ ቅያሪዎችን አድርገው የገቡት ዩጋንዳዎች በበኩላቸው በ63ኛው ደቂቃ ኢካፑት ፋዚላ በፈጠረችው ጥሩ የግብ ማግባት እድል ግብ ለማስቆጠር ቀርበው ነበር።

ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ በአንፃራዊነት ከሜዳቸው ወጥተው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ዩጋንዳዎች ትተውት በሚወጡት ሜዳ ላይ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ኳሶችን እያገኙ አደጋዎችን ሲፈጥሩባቸው ተስተውሏል። በ75ኛው ደቂቃ ሴናፍ ለሰርካዲስ አቀብላት ሰርካዲስ በመታችው ነገር ግን የዩጋንዳ ተከላካዮች ባወጡት ኳስ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ተጨዋቾቹ ከደቂቃ በኋላ በፈጠሩት እድል ግብ አስቆጥረዋል። ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ መስከረም ካንኮ ሞክራው ተከላካዮች ሲመልሱት በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረችው ሎዛ አበራ የቡድኑን ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በቀላሉ ዩጋንዳዎች ትተውት የወጡትን ሜዳ በመጠቀም እድል ያገኙት ተጨዋቾቹ ሴናፍ አመቻችታ ባቀበለቻት ኳስ ሰርካዲስ ሶስተኛ ጎል አስቆጥራ መሪነታቸውን አስፍተዋል። ሶስት ግቦች ከተቆጠረባቸው በኋላ ጫና ማሳደር የጀመሩት ዩጋንዳዎች ተቀይራ ገብታ ጥሩ ስትንቀሳቀስ በነበረችው ኢካፑት ፋዚላ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል በመድረስ የግብ እድሎችን ፈጥረዋል ።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ ሰዓት ሊታይ ሲል ከርቀት የቅጣት ምት ያገኙት ዩጋንዳዎች በአሉካ ግሬስ አማካኝነት አጋጣሚውን ወደ ጎል ለመቀየር መተውት ታሪኳ ደቢሶ በራሷ ላይ አስቆጥራ የመጀመሪያ ግብ አግኝተዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ትኩረታቸውን አጥተው የነበሩት የኢትዮጵያ ተጨዋቾች የመጀመሪያው ግብ ከተቆጠረ ከአንደኛ ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ናሱና አሲፋህ በጭማሪው ደቂቃ የመታችው የመዓዘን ምት በግምባር ተገጭቶ ሲመለስ ድጋሜ አግኝታው ወደ ግብ ስትመታው መረብ ላይ አርፎ ሁለተኛ ዩጋንዳዎች ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ጨዋታው 3ለ2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡