ነገ በሚደረገው የቡና እና ደደቢት ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች አንስተናል።
በሳለፍነው ሳምንት ከተከታታይ ሽንፈቶቻቸው በማገገም ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ነገ በአዲስ አበባ 11፡00 ላይ በ17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ እርስ በርስ ይገናኛሉ። ወትሮውም መልካም ፉክክር የሚታይበት እና ጎሎች የማያጡት የቡድኖቹ ጨዋታው ካሳኳቸው ድሎች ጋር ተዳምሮ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደሚታይበትም ይጠበቃል።
በድንገት ከዋንጫ ፉክክሩ ቁልቁል የተንሸራተተው ኢትዮጵያ ቡና አምስት ጨዋታዎችን በመደዳ ከተሸነፈ በኋላ ነው ወልዋሎን መርታት የቻለው። የነገው ጨዋታም ቡድኑን እስከ ስድስተኛነት ከፍ የማድረግ አቅም ስለሚኖረው ወሳኝነቱ የጎላ ነው። የተለመደውን በአጫጭር ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ አጨዋወታቸውን ለመተግበር የሚሞክሩት ቡናዎች ረጃጅም ኳሶችንም ሲጠቀሙ ይታያል። ይህ ሁኔታ ይበልጠኑ ጥንቃቄን የሚመርጥ ቡድን ሲገጥማቸው የሚታይ ከመሆኑ አንፃር ነገም ሊደገም እንደሚችል መገመታል። እንደ ወልዋሎው ጨዋታ ሁሉም ተሻጋሪ ኳሶች ለቡድኑ ተጨማሪ የግብ ዕድል መፍጠሪያ አማራጮች የመሆን አጋጣሚም ሊኖራቸው ይችላል። ተመስገን ካስትሮ ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ኢስማ ዋቴንጋን በጉዳት ምክንያት የሚያጡት ቡናማዎቹ በድሉ ምክንያት ተደጋጋሚ ለውጦች የሚያደርጉበት የመጀመሪያ አሰላለፍ እምብዛም እንደማይለውጡ ሲጠበቅ በዚህም በድግግሞሽ ለሚመጣው የተሸለ የቡድን መግባባት ሊረዳቸው ይችላል።
ከአዲሱ አማካያቸው ሮበን ኦባማ ጋር የተለያዩት ደደቢቶች አሁንም በሊጉ ግርጌ ቢገኙም በደቡብ ፖሊስ ላይ ባሳኩት ድል ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ነጥብ ከማግኘታቸው ባለፈ ከሽረ ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ስምንት ዝቅ በማድረግ መጠነኛ ተስፋ አግኝተዋል። የነጥብ ልዩነቱን ከዚህ በታች ለመቀነስ ደግሞ ነገ ከመዲናዋ ሙሉ ነጥብ ይዘው መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ከአማካዩ አቤል እንዳለ ጉዳት ውጪ ሌላ ተጫዋች የማያጡት ሰማያዊዎቹ ወደ ኳስ ቁጥጥር ያደላ አቀራረብ ቢኖራቸውም ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት ይዘው የሚገቡ ይመስላል። ይህን ለማድረግ ግን ዝግታ ይሚታይበትን የቡድኑን የማጥቃት ሽግግር በተለይም መድሀኔ ብርሀኔ እና ዳግማዊ አባይ በሜዳው ቁመት በሚጣመሩበት የቀኙ የቡድኑ የማጥቃት ወገን ፍጥነቱን መጨመር አስፈላጊው ይሆናል። ጨዋታው የቡድኑ የአማካይ ክፍል ተጫዋቾችም የቁጥር ብልጫ ሊያገኙ ከሚችሉበት የተጋጣሚያቸው ተመሳሳይ ክፍል አንፃር የተሻሉ ቅብብሎችን በመከወን ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት የማድረስ ብቃታቸው የሚፈተንበት ይሆናል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች 19 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ደደቢት 10 በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ ኢትዮጵያ ቡና 7 ጊዜ አሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በርካታ ጎሎችን በሚያስተናግደው የሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት 59 ጎሎች ሲቆጠሩ ደደቢት 32 ፣ ኢትዮጵያ ቡና 27 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።
– በግንኙነቶቻቸው በአንድ አጋጣሚ (2009) ላይ ያለ ጎል አቻ ከመለያየታቸው በቀር በሌሎቹ ጨዋታዎች ሁሉ ግቦች ተስተናግደዋል።
– ዘንድሮ አዲስ አበባ ላይ አስር ጨዋታዎችን ያከናወነው ኢትዮጵያ ቡና ዕኩሌታውን በድል ሲወጣ የመጨረሻዎቹን ሦስት ጨዋታዎች በሽንፈት ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቋል።
– ከሜዳው ውጪ ያደረጋቸውን ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ የተሸነፈው ደደቢት ማስቆጠር የቻለውም አንድ ግብ ብቻ ነው።
ዳኛ
– እስካሁን በመሀል ዳኝነት በመራቸው ሦስት ጨዋታዎች 11 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው ባህሩ ተካ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊጉ ያደገው አርቢትሩ በሌሎች ሰባት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን አገልግሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)
ወንድወሰን አሸናፊ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን – አህመድ ረሺድ
ሄኖክ ካሳሁን
አማኑኤል ዮሀንስ – አስራት ቱንጆ
ካሉሻ አልሀሰን
ሁሴን ሻቫኒ – አቡበከር ናስር
ደደቢት (4-2-3-1)
ሙሴ ዮሐንስ
መድሀኔ ብርሀኔ – አንቶንዮ አቡዋላ – ኃይሉ ገብረየሱስ – ኄኖክ መርሹ
የዓብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው
ዳግማዊ አባይ – ዓለምአንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ
ፉሴይኒ ኑሁ