ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ደደቢትን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሻለ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሃ ግብር ደደቢትን የጋበዘው ኢትዮጵያ ቡና ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ አሸንፏል።

በተስተካካይ መርሀ ግብር የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በድል ከተመለሱባቸው የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አንድ አንድ ቅያሪን ብቻ አድርገዋል። በዚህም መሰረት ወልዋሎን አሸንፎ የተመለሰው ኢትዮጵያ ቡና ኃይሌ ገብረትንሳይን ተጠባባቂ በማድረግ እያሱ ታምሩን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ሲያስገባ ደቡብ ፖሊስን የረታው ደደቢት ደግሞ ዳግማዊ ዓባይን በማሳረፍ ዳዊት ወርቁን ተጠቅሟል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ያስመለከቱን ሁለቱ ቡድኖች በ10 ደቂቃ ውስጥ አንድ አንድ ጎሎችን አስቆጥረው የጨዋታውን ጅማሮውን አሳምረዋል። ጨዋታው ገና እንደተጀመረ ከመሃል ሜዳ ሲመታ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ በወጣው ኳስ የመጀመሪያ የመዓዘን ምት ያገኙት ደደቢቶች አጋጣሚውን ዓለምአንተ አሻምቶት እንዳለ ከበደ በግምባሩ በመጭረፍ ወደ ግብ ቀይሮ ገና በጅማሮው መሪ ሆነዋል። ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከጅምሩ የተወሰደባቸውን የግብ የበላይነት ለማስተካከል ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል። በ8ኛው ደቂቃም ከቅጣት ምት በተሻገረ ኳስ የቡድኑ አምበል አማኑኤል ዮሐንስ ጥብቅ ኳስ መቶ አቻ ለመሆን ሞክረዋል።

በተደጋጋሚ ወደ ደደቢቶች የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩት ቡናዎች ብዙም ሳይቆይ በ10ኛው ደቂቃ ክሪዚስቶም ንታምቢ ከአስራት ቱንጆ የተሻማውን የቅጣት ምት በግምባሩ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል። አቻ ከሆኑ በኋላም ግብ ለማስቆጠር ጥረታቸውን ያላቋረጡት ቡናማዎቹ ከሁለት ደቂቃ በኋላ አቡበከር ናስር በፈጠረው ጥሩ እድል ለግብ ቀርበው ነበር። በአምስት ተከላካይ ወደ ሜዳ የገቡት ደደቢቶች በቀጥተኛ አጨዋወት ከሚያገኙት አጋጣሚዎች ውጪ እምብዛም ወደ ኢትዮጵያ ቡናዎች የግብ ክልል ሲደርሱ አልታየም። በ16ኛው ደቂቃ ግን ከመዓዘን ዓለምአንተ ካሳ ያሻገረውን ኳስ አንቶኒዮ አቡዋላ አግኝቶ በቀጥታ በመሞከር ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል።

ሁለቱ ቡድኖች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በስታዲየሙ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት መቀዛቀዝ የጀመረው ጨዋታው በተለይ ቡድኖች የሚያደርጉትን የኳስ ቅብብል ሜዳው ውሃ በማቆሩ ሲበላሽ ተስተውሏል። ከሜዳው አለመመቸት ምክንያት እንደ አጀማመሩ ያልቀጠለው ጨዋታው የግብ ሙከራዎችን ከማስተናገድ ይልቅ እየተቆራረጠ ውበቱ ደብዝዟል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ቡናዎች የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ደደቢቶች በ36ኛው ደቂቃ በቅብብል ስህተት በተገኘ ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው መክኖባቸዋል። ከዚህ አጋጣሚ በተጨማሪ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ፉሴይኒ ኑሁ በግራ መስመር በኩል ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመታው ኳስ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ አድርገዋል። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ አጀማመራቸው ሳይዘልቁ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቃራኒ መህክ በነበረው የሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፍክክር አልባ ነበር። ነገር ግን ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጨዋታው እየተሟሟቀ በመሄድ ጥሩ ፉክክር አስመልክቷል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ከግብ ክልላቸው ወጣ ብለው ለመጫወት ያሰቡት ደደቢቶች በ56ኛው ደቂቃ ፉሴይኒ ኑሁ በመልሶ ማጥቃት የተገኘን ኳስ በመጠቀም በሞከረው ሙከራ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ በተራቸው ሙከራ የሰነዘሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች አቡበከር አቀብሎ አማኑኤል ባመከነው ኳስ ወደ ግብ ቀርበዋል። በ56ኛው ደቂቃ የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ደደቢቶች በ62ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጥሩ እድል በአምበላቸው የዓብስራ ተስፋዬ አማካኝነት ፈጥረው ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ አምክኖባቸዋል።

ሲጥል የነበረው ከባድ ዝናብ በመጠኑ ካቆመ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች በመጨመር ደደቢቶች ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። በተቃራኒው በመጀመሪያ ካሰለፉዋቸው ሁለት አጥቂዎች አንዱን በማስወጣት የመከላከል ባህሪ ያለው ተጨዋች ያስገቡት ደደቢቶች ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ ይበልጥ መከላከሉ ላይ በማተኮር አፈግፍገው ተጫውተዋል። አሁንም ግብ ለማስቆጠር ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ቡናዎች በ67ኛው ደቂቃ የተገኘን የመዓዘን ምት አህመድ ረሺድ በግምባሩ በመግጨት በሞከረው ሙከራ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሐሰን ሻባኒ በመስመር ላይ አጨዋወት የተሳሳተውን ኳስ ያገኙት ደደቢቶች ነቅለው በመውጣት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የመስመር ተከላካዮቻቸውንም በማጥቃት አጨዋወት ያሳትፉ የነበሩት ቡናዎች በ77ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር በአግባቡ ተጠቅሞበት ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህች ጎል ይበልጥ የተነቃቁት የአሰልጣኝ ገዛኸኝ ተጨዋቾች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ኳስን ተቆጣጥረው በትግስት ለመጫወት ሞክረዋል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም አስራት ቶንጆ ያሻማው የመዓዘን ምት ሻባኒ ገጭቶ አግዳሚውን ሲመለስ ያገኘው አህመድ ረሺድ ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል አስቆጥሮ መሪነታቸውን አስፍተዋል። ከሶስተኛው ጎል በኋላ የልብ ልብ የተሰማቸው ተጨዋቾቹ ኳስን ተቆጠቀጥረው ጨዋታውን 3-1 መጨረስ ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች 28 ነጥቦችን በመያዝ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ተጋባዦቹ ደደቢቶች ባሉበት 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡