የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 3-1 ደደቢት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢትን አስተናግዶ 3-1 በሆነ ውጤት ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

“አስፈላጊ ጨዋታ ስለነበር ጥሩ ውጤቱ አምጥተናል ” ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ድሉ

የጨዋታው ገፅታ ጥሩ ነበር። ምክንያቱም እኛ ይሄን ነጥብ እንፈልገው ነበር፤ ያለንን ደረጃ ምናሻሻልበት ነበር። በዛ ላይ ደግሞ ተስተካካይ ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር ተደራረቢም ነበር። ወደ ቀጣዩ ጨዋታ ለመሄድ ደግሞ አስፈላጊ እና ውድ የሆነ ጨዋታ ስለነበር ጥሩ ውጤቱ አምጥተናል። በመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ባልታሰበ ሰዓት ላይ ነው ጎል የተቆጠረብን። ያ ደግሞ ተጫዋቾቹ ላይ የፈጠሩ ጫናዎች አሉ። በሂደት ግን የተሻለ ነገር ሰርተናል ፡፡

በተከላካይ ክፍሉ ላይ ስለታየው የመከላከል ድክመት

በዚህ ሜዳ ላይ ይህን አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ቢከብድም እንደቡድን የተሻለ ነገር አድርገናል። ይህንን ደግሞ በሂደት የምናስተካክላቸው ናቸው፡፡ እኛ በሶስተኛ ሜዳ እና አማካዩ ላይ አብዝተን የምንጫወተውን የምንቀጥልበት ይሆናል። ተከላካዮቹ ላይ በእርግጥ መስተካከል የሚገባው ነገር አለ። እሱን ደግሞ አርመን እንመጣለን፡፡

“ዳኛው ነው ጨዋታውን የቀየረው” ዳንኤል ፀሐዬ – ደደቢት

ስለ ጨዋታው

የመጀመሪያው በአየር ፀባዩ ምክንያት ይሄ ጥሩ ነው ያ መጥፎ ነው የምንልበት አይደለም። በአጠቃላይ ዝናቡ አጨዋወታችን ቀይሮታል። እኛ ደግሞ ዝናቡ እስኪቆም ጨዋታው ይቁምልን ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ እግር ኳስ ነው፤ ህዝቡም ተዝናንቶበት እንዲወጣ በትክክለኛው መንገድ ተጫውተን ለመውጣት ነበር ያሰብነው። እንድንወርድ ያደረገን ደግሞ የአየሩ ጉዳይ እንጂ የአቅም ወይም ሌላ ችግር አይመስለኝም። ይዘነው የገባነው አጨዋወት ማጥቃት ላይ ያተኮረ ነበር። ምክንያቱም በሶስት ተከላካይ ነበር የምንጫወተው። ይህ ደግሞ በመከላከል ላይ አተኩረን የምንጫወትበት አይመስለኝም። አየሩ ከተቀየረ በኋላ ረጃጅም ኳሶች ናቸው ከቡና የሚመጡት። ይሄን ለማምከን ደግሞ ኮሪደሩን መዝጋት ነበረብን፤ ያንን ለማድረግ ሞከረን ስንጫወት የነበረው በማጥቃት ብቻ ለመጫወት ነበር። ለመከላከል ብለን አልመጣንም። ነጥብ ይዘን እንሄዳለን ብለን አስበን ነበር። ዝናቡ ባይኖር ኖሮ ውጤቱ ይሄ አይሆንም።

ስለተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት እና ስለዳኝነቱ

ዳኛውን ብዙ ማለት አልፈልግም፤ ስለ ዳኛ አላወራም። ምክንያቱም ከኔ በላይ እናንተ ያያችሁት ነገር ስላለ። የተሰጠብንን ፍፁም ቅጣት ምት ከኛ ይልቅ እናንተ ብትፈርዱ ይሻላል። በኔ እይታ ሊታየኝ ባይችልም ተጫዋቾቹ ግን ያን ያክል ስሜታዊ አይሆኑም ነበር። ለኔ ምክንያት ጠብቆ እንደሰጠ አድርጌ ነው የማስበው። ምክንያቱም የቡናዎች መነቃቃት የመጣው ከጎሉ በኋላ ነው። ፍፁም ቅጣት ምቷን ለራሱ ለዳኛው ህሊና እተወዋለው። ዳኛው ነው ጨዋታውን የቀየረው፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡