ከ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ዛሬ በብቸኝነት የሚደረገው የደቡብ ፖሊስ እና ወልዋሎ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ባሳለፍነው ሳምንት በተመሳሳይ በትግራይ ስታድየም ባደረጓቸው ጨዋታዎች የ1-0 ሽንፈቶች ያስተናገዱት ደቡብ ፖሊስ እና ወልዋሎ ዛሬ በሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ 09፡00 ላይ በ19ኛ ሳምንት መርሀግብር ይገናኛሉ።
አራት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ የነጥብ ድምራቸውን ከአምስት ወደ አስራሰባት ማሳደግ ችለው የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በደደቢት በደረሰባቸው ሽንፈት ለአንድ ሳምንት ወጥተው ወደነበሩበት ወራጅ ቀጠና ተመልሰዋል። ዛሬ በፉክክሩ ውስጥ ካሉ ቡድኖች መካከል በቅድሚያ ጨዋታቸውን እንደማድረጋቸውም ሙሉ ነጥቦችን ማሳካት እስከ 11ኛ ደረጃ ከፍ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጨዋታው በድኑ ተከታታይ ድሎቹን ተከትሎ የታየበት መነቃቃት ጨርሶ እንዳይከዳውም እጅግ ወሳኝ ይሆናል። በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርተው በማጥቃት የሚጫወቱት ደቡብ ፖሊሶች በተለይም በሦስቱ ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው አስር ግቦች በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩ መሆናቸውን ላስተዋለ ዛሬም የመስመር አጥቂዎቻቸውን ፍጥነት ተጠቅመው ከፍ ያለ ጫና በመፍጠር ጨዋታውን እንደሚጀምሩ መገመት አያዳግተውም። የየተሻ ግዛው ከጉዳት የአበባው ቡታቆ ደግሞ ከቅጣት መመለስም በሁለቱ ክንፎች ለቡድኑ ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆነው ይታሰባል።
ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኃላ ከትግራይ ስታድየም ለሚወጡት ወልዋሎዎች ጨዋታው በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዮሀንስ ሳህሌ ስር የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ፈተናቸው ይሆናል። 24 ነጥብ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው የሰባት ነጥቦች ርቀት ቢኖረውም ልዩነቱን ይበልጥ አስፍቶ መሀል ላይ ለመደላደል ከሀዋሳው ጨዋታ ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት እንደሚፋለም ይጠበቃል። ከአሰልጣኝ ዮሀንስ አቀራረብ እንዲሁም ተጋጣሚው በሜዳው ይዞት ሊገባ ከሚችለው ማጥቃት ላይ የተመሰረተ ዕቅድ አንፃር ሲታይ ወልዋሎ በመጀመሪያው ዙር ከሜዳው ውጪ ያደርግ እንደነበረው ክፍት ላይሆን ይችላል። ወልዋሎዎች ጥንቃቄን በመምረጥ የቅርፅ ለውጥም ሊያደርጉ በሚችሉበት በዚህ ጨዋታ በፊት አጥቂነት ከሪችሞን ኦዶንጎ ይልቅ ለአዲስ ፈራሚያቸው ክርስቶፈር ችዞባ እየሰጡት ያሉትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል ይቀይሩ እንደሆንም ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ከቀናት በፊት ከአማካዩ አስራት መገርሳ ጋር የተለያየው ቡድኑ ዛሬ እንየው ካሳሁንን በቅጣት አፈወርቅ ኃይሉን ደግሞ በጉዳት የማይጠቀም ይሆናል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን የመቐለው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወልዋሎ በኤፍሬም አሻሞ ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል።
– ሀዋሳ ላይ አስር ጨዋታዎችን ያደረገው ደቡብ ፖሊስ ሦስቴ ድል ሲቀናው በቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች ግን ምንም ነጥብ ማሳካት አልቻለም።
– በሰባት አጋጣሚዎች ከትግራይ ስታድየም ውጪ የተጫወቱት ወልዋሎዎች ሦስት ጊዜ በሽንፈት ሲመለሱ ሁለት የአቻ እና ሁለት የድል ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።
ዳኛ
– በመጀመሪያው ዙር አራት ጨዋታዎችን ዳኝቶ ዘጠኝ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን የሰጠው ሀብታሙ መንግስቴ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል። በሦስት ጨዋታዎች ላይ አራተኛ ዳኛ መሆን የቻለው አርቢትሩ ከዚህ በፊት ደቡብ ፖሊስን ከደደቢት ያጫወተ ሲሆን ወልዋሎን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዳኝ ይሆናል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)
ሀብቴ ከድር
አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – አዳሙ መሀመድ – አበባው ቡታቆ
ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ብሩክ አየለ
የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – በረከት ይስሀቅ
ወልዋሎ ዓ /ዩ (4-2-3-1)
አብዱላዚዝ ኬይታ
ዳንኤል አድሃኖም – በረከት ተሰማ – ደስታ ደሙ – ብርሀኑ ቦጋለ
ብርሃኑ አሻሞ – አማኑኤል ጎበና
ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – አብዱርሀማን ፉሴይኒ – ኤፍሬም አሻሞ
ክርስቶፈር ችዞባ