ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ዛሬ አንድ ጨዋታ የተስተናገደበት የሊጉ 19ኛ ሳምንት ነገ ደግሞ ሀዋሳ እና ባህር ዳርን ያገናኛል።

በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ ወጣ ገባ ሲሉ የከረሙት ሀዋሳ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ በሦስት ነጥቦች ልዩነት እንዳሉ ሆነው ነገ 09፡00 ላይ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ይፋለማሉ። ሁለተኛው ዙር ከገባ ከድል ጋር መገናኘት የተሳነው ሀዋሳ ከፋሲል ነጥብ ከመጋራቱ ውጪ ወልዋሎ እና ወላይታ ድቻን በገጠመባቸው የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ተሸንፎ ተመልሷል። 25 ነጥብ ላይ መቆሙም ከሊጉ መሪነት እየተንሸታተተ ሄዶ 10ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ሆኗል። ሜዳቸው ላይ የተሻለ ጥንካሬን የሚያሳዩት ሀዋሳዎች በነገው ጨዋታ ወደ ድል ለመመለስ የሚልሙ ሲሆን በዋነኝነት አሁንም ከመስመር ተመላላሾቻቸው በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ በመመስረት በሙሉ ኃይላቸው አጥቅተው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል። በጨዋታው ሀይቆቹ ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት ዓዲስአለም ተስፋዬ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን በወልዋሎ እና ድቻ ጨዋታ በተመለከቱት ቀይ ካርድ ቅጣት ምክንያት የማይጠቀሙ ይሆናል፡፡

ከዋንጫ ተፎካካሪዎቹ መካከል ያሉትን ጊዮርጊስ እና ሲዳማን መርታት የቻሉት ባህርዳሮች በ28 ነጥቦች ወደ አምስተኝነት ከፍ ብለዋል። በመጀመሪያው ዙር መገባደጃ ላይ ያሳዩትን መዋዥቅም ያስተካከሉ ይመስላል። ሆኖም ከሜዳ ውጪ ያላቸውን ሪከርድ ከማስተካከል አንፃር የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው። የተጋጣሚያቸውን የመስመር ጥቃት በመመከት በሁለቱ ክንፎች በፈጣን ሽግግር ግብ ለማግኘት እንደሚጥሩ የሚጠበቁት የጣና ሞገዶቹ ፈተና ሊሆንባቸው የሚችለው ዋናው ጉዳይ የስብስባቸው መዳከም ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ በሜዳው ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ ባሸነፈበት ጨዋታ ያልተሰለፈው ሣለአምላክ ተገኝ አሁንም ከጉዳቱ ባለማገገሙ ወደ ሀዋሳ ያልተጓዘ ሲሆን የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል አለሙ በተመሳሳይ በጉዳት እንዲሁም ሁሉንም የሊጉን ጨዋታዎች የተጫወተው የተከላካይ መስመር ተሰላፊው አቤል ውዱ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሳቢያ አይሰለፍም። አሰልጣኝ ጻውሎስ ሦስት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በነገው ጨዋታ ቢያጡም በኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ተከታታይ ጨዋታዎች ያመለጣቸው ወንድሜነህ ደረጄ እና ምንተስኖት አሎ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ በመሆናቸው መጠነኛ አማራጭን ያገኛሉ።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በአራተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር የተከናወነው የቡድኖቹ የመጀመሪያ የእርስ በርስ ግንኙነት ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

– ሀዋሳ ላይ አስር ጨዋታዎችን ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ስድስቱን አሸንፈው በሦስቱ አቻ ሲለያዩ ፋሲልን ባስተናገዱበት የመጨረሻ ጨዋታቸው ነጥብ ተጋርተዋል።

– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በሦስቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰ ሲሆን አራት ሽንፈቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ተፈሪ አለባቸው በመሀል ዳኝነት ይመራዋል። እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች በመሀል በሌሎች አምስት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት የተመደበው ተፈሪ 33 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ ሁለት የቀይ ካርዶች እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳህ

ወንድማገኝ ማዕረግ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አስጨናቂ ሉቃስ – ሄኖክ ድልቢ– ታፈሰ ሰለሞን – ደስታ ዮሀንስ

አዳነ ግርማ – እስራኤል እሸቱ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሐሪሰን ሄሱ

ማራኪ ወርቁ – አሌክስ አሙዙ – ወንድሜነህ ደረጄ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ዜኔው ፈረደ – ፍቃዱ ወርቁ – ግርማ ዲሳሳ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡