ሪፖርት | ወልዋሎ ከአቻ እና ሽንፈት በኋላ በፕሪንስ ግሩም አጨራረስ ወደ ድል ተመልሷል

ባለፈው ሳምንት በትግራይ ስታዲየም ሽንፈት ያስተናገዱት ደቡብ ፖሊስ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ሀዋሳ ላይ ያገናኘው የ19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ ደቡብ ፖሊሶች በ18ኛው ሳምንት በደደቢት ከተሸነፉበት ጨዋታ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ዘሪሁን አንሼቦ፣ ብሩክ አየለ እና ብርሀኑ በቀለን በማስወጣት ዘነበ ከድር፣ የተሻ ግዛው እና ኪዳኔ አሰፋን ሲጠቀሙ ወልዋሎዎች ከቡናው ሽንፈት የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ በማድረግ እንየው ካሳን በዳንኤል አድሐኖም ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በመጀመሪያዉ አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ፖሊሶች አጥቅተው መጫወትን ምርጫቸው ሲያደርጉ በአንፃሩ ወልዋሎዎች በግብ ክልላቸው በቁጥር በዝተው እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ሲከተሉ ተስተውሏል። ዘላለም ኢሳይያስን መሰረት አድርገው ከሚነሱ ኳሶች ወደ ሄኖክ አየለ እና ወደ በረከት ይስሀቅ አድልተው በሚጣሉ ኳሶች ለመጠቀም የፈለጉት ደቡብ ፖሊሶች እጅጉን ተሽለው የታዩ ቢሆኑም መከላከል ላይ መሰረት አድርገው የገቡት የወልዋሎ የተከላካይ ክፍልን ሰብረዉ ለመግባት ግን ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በ5ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አናጋው ባደግ አክርሮ የመታው እና በወልዋሎ ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰዉ ኳስ ነበር የመጀመርያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ፖሊሶች ከሶስት ደቂቃ በኋላ ዘላለም ኢሳይያስ እና በረከት ይስሀቅ በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል ወደግብ ቢደርሱም የመሀል ተከላካዩ በረከት ተሰማ አስጥሏቸዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከሳጥን ዉጭ አናጋዉ ባደግ ከየተሻ ግዛው ያገኛትን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።

የተጋጣሚያቸውን ቀዳዳ በመፈለግ ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ወደ ቀኝ እና ግራ በኩል በተሰለፉት ኤፍሬም እና ፕሪንስ የመልሰ ማጥቃት ለመጠቀም ያለሙት ወልዋሎዎች በ15ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ከቀኝ መስመር አሻምቶ ኤፎቢ ቺዞባ ወደፊት ገፋ አድርጎ ቢሞክርም ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ደቡብ ፖሊሶች የግብ አጋጣሚ መፍጠራቸውን በመቀጠል 20ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ ቦጋለ ለግብ ጠባቂው አብዱልአዚዝ ኬይታ ከሳጥን ውጭ ወደ ኋላ አቀብሎት ግብ ጠባቂው በአግባቡ ሳይለጋዉ ቀርቶ የተሻ ግዛው ጋር ደርሳ የአብዱላዚዝን መውጣት አይቶ ወደ ጎል ቢመታውም ለጥቂት ሲወጣበት በ24ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ከቀኝ ያሻማውን ኳስ በረከት ይስሀቅ ለሄኖክ አየለ በግንባሩ አቀብሎት በድጋሚ ሄኖክ አየለ በግንባሩ ሞክሮ አብዱልአዚዝ ያወጣት ለግብ የተቃረበች ነበረች። ከዚች ሙከራ በኋላ የአጋማሹን ሁለተኛ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ወልዋሎዎች በግራ መስመር በኩል ብርሀኑ ቦጋለ አሻምቶ በደቡብ ፖሊስ ተከላካዮች ስትመለስ ያገኛትን ኳስ አብዱራሕማን ፉይሴኒ ሞክሮ ግብ ጠባቂዉ ሐብቴ ከድር ተቆጣጥሮበታል፡፡

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ይህ ነው የሚባል ለግብ ሙከራ ባይደረግም በጭማሪው ደቂቃ ፕሪንስ ሰቨርኒሆ ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂዉ ሀብቴ መቆጣጠር ከቻለ በኃላ ያለ ምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው ግማሽ ወልዋሎዎች መጀመርያ ይዘውት የገቡትን የመከላከል አቀራረብ ቀይረው በመግባት ተጭነዉ ለመጫወት ሲመርጡ ባለሜዳዎቹ ደግሞ በመጀመርያው ግማሽ የነበረውን ኳስ ይዞ የመጫወት ፍላጎታቸውን በሁለተኛ ግማሽም ሲተገብሩ ተስተውለዋል። በመሀል ዳኛው እና በረዳቶች መካከል በተደጋጋሚ አለመናበብ በተስተዋለበት በዚህ አጋማሽ በተለይ የወልዋሎ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾችን በዕለቱ አንደኛ ረዳት ዳኛ ዳዊት ገብሬ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን አሰምተዋል።

በ47ኛው ደቂቃ በረከት ይስሀቅ እና ከፊት አጥቂው ሄኖክ አየለ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ገብተው በረከት ሞክሮ የወጣችበት ኳስ የመጀመርያ ሙከራ ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርጉም በቀላሉ ሲያመክነው ተሰውሏል፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይ ከአምበሉ ደስታ ጊቻሞ የተሻገረችውን ኳስ ዘነበ ከድር በቀላሉ ሲያመክን ኪዳኔ አሰፋ በ61ኛዉ ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ በረከት ይስሀቅ ቢያቀብለውም በተመሳሳይ ሊጠቀምበት አልቻለም። 66ኛዉ ደቂቃ ላይ ብሩክ ኤልያስ ያሻገራት የተመጠነች ጥሩ ኳስ በረከት ጥቂት በመዘግየቱ ምክንያት አብዱል አዚዝ ኬይታ የተቆጣጠራትም ሌላዋ ተጠቃሽ እድል ነበረች። በወልዋሎ በኩል በ58ኛው ደቁቃ ፕሪንስ ጥሩ ሙከራ ሲያደርግ በ63ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባው ኤፍሬም ኃይለማርያም ያገኛትን ኳስ ከግራ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሮ ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች በፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አማካኝነት ከቀኝ መስመር መነሻነት ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የደረሱት ወልዋሎዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረው ከጨዋታ ውጪ ከተባለባቸው ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ በደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ከኪዳኔ አሰፋ አግር በመንጠቅ ከተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ  ካለፈው በኋላ ሰብሮ በመግባት በግሩም አጨራረስ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በጭማሪዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች በጨዋታው መገባደጃ ብሩክ ኤልያስ ከ አናጋው ያገኘዉን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት በአግዳሚው የወጣበት ኳስ የሚገቀስ ነበር።

ጨዋታው በወልዋሎ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልዋሎ ከሁለት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታ በኋላ ወደ ድል በመመለስ ደረጃውን ሲያሻሽል ደቡብ ፖሊስ በአንፃሩ ሁለተኛ ተከታታይ ሽንፈት በማስተናገድ ባለበት ወራጅ ቀጠና ረግቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡