19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ሲያደርግ ሀዋሳ ላይ ወልዋሎ ባለሜዳው ደቡብ ፖሊስን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተውናል፡፡
“ከሽንፈት ስለመጣን የግድ ማሸነፍ ነበረብን” ዮሐንስ ሳህሌ – ወልዋሎ
ስለ ድሉ
ሜዳው በጣም ከባድ ነው። በተለይ ከላይ ሙቀት አለ፤ ከስርም ሙቀት አለ። ሜዳውን ተጫዋቾቹ አልለመዱትም። ከሽንፈትም ስለመጣን የግድ ማሸነፍ ነበረብን። ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን እናውቅ ስለነበር መስጠት የሚገባንን መስዋዕትነት ሰሰጥተናል። ይህን ነጥብ ማግኘታትን ወራጅ ቀጠና ከሚባለው ከማምለጥ በተጨማሪ ተጫዋቾቹ የራሳቸውን ነገር ማውጣት እንዲችሉ ያደርጋል። ከሜዳህ ውጪ ደግሞ ወጥቶ መጫወት በጣም ከባድ ነው። ሶስት ተጫዋቾች ቀይረን ጨርሰን ሁለት ተጫዋቾች ከነጉዳታቸው ነበር የተጫወቱት።
የመረጡት ታክቲክ ስኬታማነት
አዎ ተሳክቷል እላለው። ጥሩ ዕድል ሆኖ መቐለ ላይ ፖሊሶች ከደደቢት ሲጫወቱ አይተናቸው ነበር። ጋር መሀል ሜዳ ላይ ኳስ እንደሚይዙ አውቀን ነው የገባነው። መሀል ሜዳ ላይ እኛም በመጫናችን የሚጫወቱትን ጨዋታ ቆረጥንባቸው። ከዛ ከመሀል ወደ ፊት መጡ። ለኛ ደግሞ ጥሩ መግጨት የሚችሉ ተጫዋቾች ስለነበሩን አጨዋወታቸውንም በምስል ተመልክተን ምን ማድረግ አለብን ብለን ተነጋግረን ነው የገባነው። ዋናው ግን እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር አለብን ብለን ስላሰብን ልናሳካው ችለናል፡፡
“ከስህተቶቻችን ተምረን ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን” ገብረክርስቶስ ቢራራ – ደቡብ ፖሊስ
ስለ ሽንፈቱ
ጨዋታው ጥሩ ነው። እግር ኳስ የሚታይ ነገር ነው፤ መሸነፍንም መቀበል በራሱ ትልቅነት ነው። ሜዳችን ስለሆነ ብቻ እናሸንፋለን ማለት አደለም። ይሄ ያለፈው ሳምንት ጨዋታ ሽንፈት ተጫዋቾቹ ላይ የፈጠው ጭንቀት ነው። ባለፈው ጨዋታ መሸነፋችን ይሄን ጨዋታ አሸንፈን ወደ ቦታችን እንመለሳለን የሚል ጉጉት ስለነበራቸው የነገርናቸውን ነገር ለማድረግ እየጣሩ ብዙ ስህተት ሰርተናል። እነዚህ ስህተቶች ደግሞ መጨረሻ ላይ ዋጋ አስከፍሎናል። እኛ ከመስመር ከሚነሱ ኳሶች ለማጥቃት ነበር የፈለግነው፤ ያን ደግሞ አድርገናል፡፡ እነሱ የሰጡን ቦታ ጠባብ ነው፤ ይሄ ደግሞ ለሰንጣቂ ኳስ አይመችም። ቀዳዳ ለማግኘት ሁለተኛ አማራጭ ብንጠቀምም አልተሳካም።
የሚገኙ ዕድሎች በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር
ይሄ የኛ ብቻ ችግር አይደለም፤ የሀገሪቱም ችግር ነው። ይሄን ለመቅረፍ እየጣርን ነው። በአንድ ጀምበር የሚስተካከል ነገር ደግሞ የለም። ይሄ ቡድን ከበፊትም ወደ ጎል ይደርሳል፤ ግን አሁንም ጎል ማግባት ችግር አለ። ምናልባት እናንተ ከስራችሁ አንፃር ልምምዳችንን አታዩትም እንጂ ብታዩ በዚህ ክፍተታችን ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡ ግን በአንድ ጊዜ መሻሻል አይችልም፤ ሂደት ይፈልጋል። ለምሳሌ በመሀል የቀን ልዩነት ቢኖረን ኖሮ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ መሻሻሎች ሊመጡ ይችላሉ። ስለዚህ ያ ላይ ተግተን እየሰራን ነው። እናሻሻላለን ብለን እናስባለን፡፡ ይህን ደግሞ ተጫዋቾቼም ተረድተው ያሳኩታል ብዬ አምናለው። አትጠራጠሩ ከስህተቶቻችን ተምረን ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡