ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ደደቢት

በብቸኛው የአዲስ አበባ ስታድየም የነገ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ላይ ባለው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት መከላከያ እና ደደቢት ነገ በአዲስ አበባ 11፡00 ላይ ይገናኛሉ። ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድሬዳዋ ተጉዘው ነጥብ በመጋራት መጠነኛ እፎይታ ያገኙት መከላከያዎች ከአደጋው ዞን መራቅ ግን አልሆነላቸውም። በድሬው ጨዋታ ቡድኑ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ አንድ ግብ ቢያስቆጥርም በመጨረሻ ሰዓት ግብ አስተናግዶ ነበር ነጥብ የተጋራው። እንደሁል ጊዜው ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት በበርካታ ቅብብሎች ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት መከላከያዎች የተለመደው የመከላከል ችግራቸው ለደደቢት መልሶ ማጥቃት እንዳያጋልጣቸው ያሰጋል። ከዛም ባለፈ በመከላከል ወቅት አምስት ተጫዋቼችን የሚጠቀመው የሰማያዊዎቹን የመጨረሻ መስመር ማለፍ ለጦሩ ፊት አውራሪዎች ቀላል አይሆንም። ምንም አዲስ የጉዳት ዜና የሌለበት መከላከያ ወሳኝ አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ያላገገመለት ከመሆኑም ባለፈ ወደ ቀዶ ጥገና ሊያመራ መቻሉ በጎ ያልሆነው ዜና ነው።

ደቡብ ፖሊስን በመርታት ካለበት የመጨረሻ ደረጃ ቀና ማለት ችሎ የነበረው ደደቢት ባሳለፍነው ሐሙስ በተስተካካይ ጨዋታ እዚሁ አዲስ አበባ ላይ በኢትዬጵያ ቡና ሽንፈት ደርሶበታል። ነገር ግን በጨዋታው ከመሀል ሜዳ በቅብብሎች ለሚነሱ ጥቃቶች በቀላሉ ክፍተት አለመስጠቱ እና በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመድረስ ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሲፈጥ መታየቱ ለነገው ጨዋታ ጠንካራ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል የሚጠቁም ነው። በአንፃሩ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከደረሰ በኋላ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር እና የቆሙ ኳሶችን የመከላከል ችግሩ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል። ደደቢት አቤል እንዳለ እና ኩማ ደምሴን በጉዳት ሳቢያ ለነገው ጨዋታ ካለመጠቀሙ በቀር ቡናን የገጠመበትን ቡድን ይዞ እንደሚቀርብ ሲገመት በጨዋታው ተጎድቶ የወጣው ዓለምአንተ ካሳ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በፕሪምየር ሊጉ ለ19 ጊዜያት የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ደደቢት ስምንት መከላከያ ደግሞ ስድስት ድል አሳክተዋል። ደደቢት 32 ግቦችን ሲያስቆጥር መከላከያም 24 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

– አዲስ አበባ ላይ ስምንት ጊዜ የክልል ቡድኖችን የገጠመው መከላከያ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው ሦስቴ ነጥብ ተጋርቶ በአራት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

– ከመቐለ ውጪ ስምንት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት ያለምንም ነጥብ የተመለሰ ሲሆን 16 ግቦችን አስተናግዶ ማስቆጠር የቻለው ሁለት ግቤችን ብቻ ነው።

ዳኛ

– ሰባት ጨዋታዎችን ዳኝቶ 33 የቢጫ ካርዶችን የመዘዘው እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠው አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ዳዊት ማሞ – ፍሬው ሰለሞን

ዳዊት እስጢፋኖስ

ተመስገን ገብረኪዳን – ፍቃዱ ደነቀ

ደደቢት ( 3-4-1-2)

ሙሴ ዮሐንስ

ዳዊት ወርቁ – ኤፍሬም ጌታቸው – አንቶንዮ አቡዋላ

መድሀኔ ብርሀኔ – የዓብስራ ተስፋዬ – ኃይሉ ገብረየሱስ – ሄኖክ መርሹ

ዳግማዊ ዓባይ

ፉሴይኒ ኑሁ – እንዳለ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡