ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መቐለ 70 እንደርታ ከ ወላይታ ድቻ

የሊጉ መሪዎች ከወላይታ ድቻ የሚገናኙበት ጨዋታ የዛሬ ቅድመ ዳሰሳችን የመጨረሻ ትኩረት ይሆናል።

ነገ በትግራይ ስታድየም ከ09፡00 ጀምሮ ሀለቱንም የሰንጠረዡን ክፍሎች የሚነካው የመቐለ 70 እንደርታ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ይከናወናል። ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት 70 እንደርታዎች ነጥባቸውን ወደ አርባዎቹ ለማስገባት ከጫፍ ደርሰው ቆመዋል። ሠላሳ ነጥቦችን ያለማቋረጥ ከሰበሰቡባቸው አስር ጨዋታዎች በኋላ ከወልዋሎ አቻ ተለያይተው በፋሲል ከነማ ሽንፈት መቅመሳቸው ከተከታዮቻቸው ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በመጠኑ ቀንሶታል። በቀጣይ ጨዋታዎች ጫና ውስጥ ላለመግባት ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥቦችን የመስብሰብ ግዴታ ያለባቸው መቐለዎች ከፋሲሉ ጨዋታ በተለየ አኳኋን ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በዚህም ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ ገፍቶ ለመጫወት ድፍረት ያለው እና በፍጥነት ወደ ጎል የሚደርስ አይነት ቡድን ከባለሜዳዎቹ ይጠበቃል። በጨዋታው በዓመቱ መጀመርያ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ ከራቀው አቼምፖንግ አሞስ ውጪ ሙሉ ቡድን ከጉዳት ነፃ ነው። ከጉዳት ተመልሶ ላለፉት ሳምንታት በቋሚነት ልምምድ የሰራው ሳሙኤል ሳሊሶ ነገ ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎ ሲጠበቅ በተመሳሳይ ልምምድ ላይ የቆየው ስዩም ተስፋዬ መሰለፉ ጉዳይ ግን አጠራጣሪ ነው። ከዚህ ውጪ ኦሴይ ማውሊ በፋሲሉ ጨዋታ ባየው ቀይ ካርድ ምክንያት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ርቆ የሰነበተው ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ከፍ ብሎ መቀመጥ ችሏል። በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጭንቀት ውስጥ ላለመግባት ልዩነቱን ይበልጥ ለማስፋት ከሚያደርገው ጥረት አንዱ በሆነው የነገ ጨዋታም ከመቐለ ነጥብ የመውሰድ ፈተና ይጠብቀዋል። ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መምጣት በኋላ በውጤቱም ብቻ ሳይሆን በአጨዋወትም ለውጥ እያሳዩ የመጡት ወላይታ ድቻዎች ነገም የተጋጣሚያቸውን ጥቃት ከመከላከል ባለፈ ኳስ ይዘው ወደ ፊት በመግፋት ለማጥቃት የሚሞክሩ ይሆናል። ነገር ግን ቡድኑ አሁንም ከአማካይ ክፍል ወደ ፊት አጥቂዎቹ የሚያደርሳቸው የመጨረሻ ኳሶች ጥራት ላይ መሻሻሎችን ካላሳየ የመቐለን የተከላካይ ክፍል ለናለፍ ሊቸገር ይችላል። ድቻዎች ውብሸት ክፍሌ እና ውብሸት አለማየሁ እንዲሁም ሄኖክ አርፊጮን በጉዳት በነገው ጨዋታ ላይ የማይጠቀሙ ይሆናል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– መቐለ 70 እንደርታ አምና ሊጉን ሲቀላቀል ወላይታ ድቻን ባገኘባቸው ሁለት ጨዋታዎች 1-0 እና 2-0 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን ድቻ ደግሞ ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር በሜዳው የ1-0 ድልን አግኝቷል።

– ትግራይ ስታድየም ላይ 11 ጨዋታዎችን ያከናወነው መቐለ 70 እንደርታ ዘጠኝ ጊዜ አሸንፎ ሁለቴ አቻ ተለያይቷል። ከጨዋታዎቹ በስድስቱ ግብ ሳያስተነግድ ከሜዳ መውጣት ችሏል።

– ከሲዳማ ጋር ያደረጋቸውን የአዲስ አበባ ጨዋታዎች ጨምሮ ከሶዶ በወጣባቸው አስር ጨዋታዎች ምንም ድል ያላሳካው ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰውም አራት ጊዜ ብቻ ነበር።

ዳኛ
– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ወልዋሎ እና ቡናን በ18ኛ ሳምንት ባጫወተበት በዛው በትግራይ ስታድየም ይህን ጨዋታ ይመራል። በአማካይ በጨዋታ አራት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመመዘው ቴዎድሮስ እስካሁን ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ያሰናበተ ሲሆን ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችም ሰጥቷል። ከሁለቱ ተጋጣሚዎች መካከልም ወላይታ ድቻን አዲስ አበባ ላይ ከሲዳማ ኑና አጫውቶ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)

ፊሊፕ ኦቮኖ

ቢያድግልኝ ኤልያስ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ሐይደር ሸረፋ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ዮናስ ገረመው

ያሬድ ከበደ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ተክሉ ታፈሰ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – እዮብ ዓለማየሁ

ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡