የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 6ኛ ሳምንት ላይ ሲደረስ በዛሬው ዕለት በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢ/ወ/ስ አካዳሚ እና ሠላም ድል ቀንቷቸዋል።
ጎፋ ሜዳ 04:00 ላይ መከላከያን ከኢ/ወ/ስ አካዳሚ ያገናኘው ጨዋታ በአካዳሚ 2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና በጨዋታው ጅማሬ ነበር መከላከያዎች በይስሐቅ ይታገሱ አማካኝነት ከርቀት በተቆጠረች አስደናቂ ጎል ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ብዙም ሳይቆይ ጨዋታውን በመቆጣጠር ብልጫ ወስደው የተንቀሳቀሱት አካዳሚዎች በፊሊሞን ዓለም አማካኝነት አቻ ሆነዋል። ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸ በፊት አካዳሚን መምራት የቻሉበትን ሁለተኛ ጎል መልካሙ የሰጋት አስቆጥሯል።
ከእረፍት መልስ መከላከያዎች የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። አካዳሚዎችን ሦስተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም አንበሉ ከድር ዓሊ ሳይጠቀምበት በመቅረቱ ጨዋታው በአካዳሚ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በአካዳሚ ቡድን የእንቅስቃሴ መሻሻል ውስጥ አቅሙን በማሳየት ወደ ፊት ተስፋ የሚጣልበት ታዳጊ መሆኑን አማካዩ ኤርሚያስ ጌታቸው በጨዋታው ላይ ማሳየት ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ አካዳሚ ደረጃውን በመሻሻል ሁለተኛ መሆን ችሏል።
06:00 ላይ በጎፋ ሜዳ የቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ሠላምን ከአፍሮ ፅዮን ያገናኘው ሲሆን ሠላም 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ተመልሷል። ኳሱን በሚገባ በመቆጣጠር ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ሠላሞች ገና በጨዋታው ጅማሬ ነበር በፈጣን እንቅስቃሴ በአብዱልመጂድ መደድ ጎል አስቆጥረው መምራት የጀመሩት። ከደቂቃ በኋላ በሁለት ጨዋታዎች ግብጠባቂ በመሆን በአራት ጨዋታ ላይ ደግሞ የግራ መስመር አጥቂ በመሆን ሠላሞችን በጥሩ ብቃት እያገለገለ የሚገኘው እና በዛሬው ጨዋታ ላይ ግብጠባቂ በመሆን መጫወት የቻለው ትንሣኤ ያብጌታ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ጎልነት በመቀየር ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። አፍሮ ፅዮኖች አራት ተጫዋቾችን በፍጥነት በመቀየር ድክመታቸውን በማሻሻል ኤርሚያስ አበበ ከርቀት ጎል በማስቆጠር የጎሉን መጠኑን ማጥበብ ችለዋል።
ከእረፍት መልስ ጥሩ ፍክክር ብንመለከትም ሠላሞች በአብዱልመጂድ መደድ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን 3-1 በማሸነፍ ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል።
08:00 ጃንሜዳ ላይ የተደረገው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ በ100% የድል ግስጋሴው የቀጠለው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ጥሩ የእግርኳስ ፍሰት በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ ገና የጨዋታውን መጀመር ፊሽካ የዳኛው ካሰሙበት ከሰከንዶች በኋላ ፈጣኑ አጥቂ ፀጋዬ መላኩ በአስደናቂ ሁኔታ ጎል አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ መሪ እንዲሆኑ አድርጓል።
መድኖች ተዘናግተው በነበሩበት ሰዓት ጎል ቢያስተናግዱም በፍጥነት ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ሀሞዱ ሠማን አማካኝነት አቻ መሆን የቻሉት። ለመድን ተከላካዮች ፈተና ሆኖ የዋለው አጥቂው ፀጋዬ መላኩ ከመሐል ሜዳ ተከላካዮችን በመቀነስ በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ሌላ አስደናቂ ጎል ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የቻለው።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ከመጀመሩ አስቀድሞ ኢትዮጵያ መድኖች የተጫዋች ተገቢነት ክስ ያሲያዙ ሲሆን ጎል ፍለጋ ጥረት ያደረጉ ባለበት ሰዓት ለፈረሰኞቹ ሦስተኛ ለራሱም ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል ፀጋዬ መላኩ አስቆጥሯል። ፀጋዬ በውድድሩ እስካሁን ስምነተኛ ጎሉ ሆኖ ሲመዘገብ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱን ከአዳማው ፍራኦል ጫላ ጋር መጋራት ችሏል። ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።
የውድድሩ 6ኛ ሳምንት ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ነገ በጃንሜዳ ሲቀጥሉ 04:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክከ አዳማ ከተማ፣ 06:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀሌታ የሚጫወቱ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡