በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬም ሲቀጥል ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ባህር ዳር ከተማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀይቆቹ ባሳለፍነው ሳምንት ሶዶ ላይ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ውስጥ ሶሆሆ ሜንሳህ፣ አስጨናቂ ሉቃስ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን እና ቸርነት አውሽን በማስወጣት ተክለማርያም ሻንቆ ወንድማገኝ ማዕረግ፣ እስራኤል እሸቱ እና ደስታ ዮሀንስን በመጀመርያ አሰላለፍ ሲጠቀሙ ሲዳማ ቡናን በ18ኛው ሳምንት በሜዳቸው የረቱት ባህር ዳሮች ሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ አድርገዋል፡፡ አቤል ውዱን በወንድሜነህ ደረጀ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በኤልያስ አህመድ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
በመጀመርያው ግማሽ ሁለቱም ቡድኖች አጥቅተው ለመጫወት መርጠው የነበሩ ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ግን ሀዋሳ ከተማ በመጀመርያው ግማሽ ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል። አጨዋወታቸውን በተለይ በመሐል ሜዳ ከታፈሰ ሰለሞን በሚነሱ ኳሶች ላይ ትኩረት ከማድረጋቸው በተጨማሪ በቀኝ እና ግራ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ከመከላከሉ ይልቅ ወደ ፊት በተሻጋሪ ኳሶች በዳንኤል እና ደስታ ለመጫወት ያለሙት ባለሜዳዎቹ የዳንኤል ደርቤ ገና በጊዜ በጉዳት መውጣት ቡድኑን ላሰቡት አጨዋወት ስጋት ቢሆንባቸውም እጅጉን በርካታ ሙከራዎችን ግን ማድረግ ችለዋል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ በግራ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክሊሉ ተፈራ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘችውን የቅጣት ምት ደስታ ዮሀንስ በቅርብ ርቀት ላይ ለነበረው ታፈሰ ሰለሞን አቀብሎት ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ሀሪስተን ሄሱ በአስደናቂ ብቃቱ ያወጣበት ኳስ የሀዋሳዎች የማጥቃት ጅማሮ በጠንካራ ሙከራ የጀመረበት ነበር። በ7ኛው ደቂቃ በግራ አቅጣጫ አክሊሉ ተፈራ ያሻገረውን ኳስ የባህርዳር ተከላካዮች እና የግብ ጠባቂዉን ሀሪሰን አለመናበብ አይቶ እስራኤል እሸቱ ተቆጣጥሮ አክርሮ ሲመታ አወጣለሁ ብሎ አሌክስ አሙዙ በራሱ ግብ ከመረብ አሳርፎ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
ተጭነው በመጫወት ተጨማሪ ግብ ለማግባት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት ሀይቆች በ22ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ አዳነ ግርማ መጥኖ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በግራ የሳጥኑ ቦታ ደስታ ዮሀንስ የሞከራት ኳስ ለጥቂት በአግዳሚ የወጣችበት እና ከአራት ደቂቃዎች በኋላ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ታፈሰ ሰለሞን ኳስ ከሚጀመርበት መሀል ሜዳ አንስቶ ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ ግብ ብቻውን ደርሶ በቀላሉ ለቡድን ጓደኞቹ አቀበለ ሲባል ራሱ መቶት ሀሪስተን ሲተፋው ተቀይሮ የገባው ምንተስኖት አበራ አግኝቶ በድጋሚ ሞክሮ ግብ ጠባቂው በድጋሚ ይዞበታል፡፡
ከቅጣት ምት መነሻነት ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ መስመር ሰብረው በመግባት የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት የጣና ሞገዶች በመጀመርያው ግማሽ የመጀመርያ ሙከራቸውን ያደረጉት ግርማ ዲሳሳ በ17ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ቀኝ ለዜናዉ ፈረደ አመቻችቶ ያቀበለው ኳስ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መትቶ በወጣችበት ነበር። 35ኛው ደቂቃ ከባህርዳር የግብ ክልል ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በረጅሙ የተሻማችዉን ኳስ ላውረንስ ላርቴ በአግባቡ ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ በቅርብ ርቀት ላይ የነበረወረ ዜናው ፈረደ ኳሷን ከእግሩ በመንጠቅ ለፍቃዱ ወርቁ አቀብሎት ፍቃዱ ወደ ውስጥ እየገፋ ገብቶ ኳስና መረብ በማገናኘት ባህርዳር ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ጎል በተጨማሪ ፍቃዱ ወርቁ ተጨማሪ ዕድልንም አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻዎች አስር ደቂቃዎች ዳኞች በሚሰሯቸው ተደጋጋሚ ስህተቶች ምክንያት የሀዋሳ እና የባህርዳር ተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሉ በሙሉ ተቃውሟቸው ሲያሰሙ ተስተውሏል። የባህርዳር ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እና ቡድን መሪው ከዕለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው እና ረዳቱ ሸዋንግዛው ጋር በተደጋጋሚ ሰጣ ገባ ውስጥ እየገቡ ለጨዋታ በየመሀሉ መቆራረጥ ምክንያቶች ነበሩ። ይሁንና የእለቱ ዳኛ ለመውሰድ የሞከራቸው እርምጃቸው ምላሻቸው እምብዛም በመሆኑ በሁለተኛው አጋማሽ ለተፈጠሩት ተቃውሞች መነሻ ሆነዋል፡፡
የሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን ባህር ዳሮች ከመጀመርያው ግማሽ ተሻሽለው ሲቀርቡ ባለ ሜዳዎቹ ደግሞ ወጣ ገባ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በ48ኛው ደቂቃ ኤልያስ አህመድ ሳጥን ውስጥ ኳስ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ውጭ ለነበረው አስናቀ ሞገስ በጥሩ ሁኔታ አቀብሎት አሰናቀ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ተ/ማርያም ሻንቆ ሲቆጣጠርበት ከዚህች ሙከራ በኋላ ሀይቆቹ ከግባቸው ኳስ መስርተው በፍጥነት ባህርዳር ግብ ላይ በመድረስ ከደስታ ዮሀንስ ያገኛትን ጥሩ ኳስ በፍጥነት ግብ ለማስቆጠር የፈለገው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ተቆርጣ ወደ ውጭ ወጥታበታለች። ታፈሰ ሰለሞን ከመሀል ሜዳ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ደስታ ዮሀንስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ የግቡ ጠርዝ ላይ በግራ እግሩ አክርሮ ሲመታው አሌክስ አሙዙ ሸርተቴ ወርዶ ያመከናትም ለግብ የተቃረበች ነበረች።
58ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ እና 60ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ ታፈሰ ሰለሞን ላይ በተሰራው ጥፋት ዳኛው ዝምታን መርጠው ሲያልፉ በዚህም ምክንያት ተጫዋቾች ወደ ሽኩቻ እንዲሁም ደጋፊዎች ደግሞ ወደ አላስፈላጊ ምላሽ አምርተው ጨዋታው ለአራት ደቂቃዎች ያክል ተቋርጦ እንደገና ጀምሯል። ሆኖም ከሜዳ ውጭ ያሉ ሽኩቻዎች በተለይ ደግሞ የባህር ዳር አሰልጣኝ ጳውሎስ እና ቡድን መሪው ከአራተኛው ዳኛ ጋር የነበረው የቃላት ምልልስ እየተደረገ እስከ ፍፃሜው የቀጠለ ነበር።
79ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ኃይሉ ከመስመር ልትወጣ ስትል ለጥቂት ተቆጣጥሮ ሰንጥቆ ለጃኮ አቀብሎ ጃኮ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ በባህር ዳር በኩል ሲጠቀስ 86ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ አዳነ ግርማ ለላውረንስ ላርቴ በግንባሩ አቀብሎት ላውረንስ የሞከራት በሀዋሳ በኩል ለግብ የተቃረበች ነበረች። ደቂቃዎች አየገፉ ሲመጣ ባህር ዳሮች ውጤቱን ለማስጠበቅ ሰዓት በማባከን ላይ ያተኮሩ ሲሆን ወንድሜነህ ደረጄ ሆን ብሎ ሰዓት ለማባከን ተኝቷል በሚል የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲመለከት ብዙም ሳይቆይ ከታፈሰ ሰለሞን ጋር ለመደባደብ በመቃጣቱ ምክንያት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
አላስፈላጊ ሰጣ ገባዎች በመቀጠል ላይ እያሉ በረጅሙ ወደ ባህርዳር የግብ ክልል የተሻገረችውን ኳስ በግብ ክልሉ ብቻውን የነበረዉ ሀሪሰተን ተቆጣጥሮ ተጎድቻለው ብሎ ሜዳ ላይ በመውደቁ ምክንያት በዚህ ደስ ያልተሰኙት ደጋፊዎች አውቆ ሰዓት ለመግደል ነው ብለው ተቃውሞ ሲያሰሙ ወደ ሜዳ ድንጋይ ሲወረወርም ተስተውሏል። በዚህም ጨዋታው ለሀያ ያህል ደቂቃዎች ተቋርጦ በድጋሚ ቢጀምርም ተጨማሪ ግቦች ሳይስተናገድበት አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡