ሪፖርት | ደደቢት ተስፋውን ሲያለመልም መከላከያ ወደ አደጋው ቀርቧል

በመዲናዋ በተደረገው የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ ደደቢት በመድሀኔ ብርሀኔ ሁለት ግቦች መከላከያን በመርታት ቀጣይ ጨዋታዎችን በተስፋ መመልከት ጀምሯል።

11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በጀመረው ጨዋታ መከላከያ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰው ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ዳዊት እስጢፋኖስን በበኃይሉ ግርማ በመተካት ለጨዋታው ቀርቧል። በደደቢቶች በኩል በተስተካካዩ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አሰላለፍ ውስጥ በተደረጉ ለውጦች ጉዳት የገጠመው ዓለምአንተ ካሳ እና እንዳለ ከበደ በአሸናፊ እንዳለ እና ዳግማዊ ዓባይ ተተክተዋል።

በመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ከጨዋታው አስቀድሞ በጣለው ከባድ ዝናብ ሜዳው ውሀ በመያዙ ቢፈተኑም በመጀመሪያው አጋምሽ ብርቱ ፉክክር አድርገዋል። በደደቢቶች ጫን ያለ ጥቃት የጀመረው ጨዋታ ቀስ በቀስ የመከላከያዎች የበላይነት እየታየበት ይቀጠለ ነበር። ደደቢቶች 10ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው ፉሰይኒ ኑሁ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በአቤል ማሞ ከተመለሰ በኋላ ለረጅም ደቂቃዎች ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተዋል። የሚያገኟቸውን ኳሶችም በፍጥነት ወደ ፊት በመጣላ ለፉሰይኒ እና ለወትሮው በቀኝ መስመር ተከላካይነት የሚታወቀው ዛሬ የአጥቂነት ሚና ለተሰጠው መድሀኔ ብርሀኔ ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክሩ ነበር። በብዛትም ከቆሙ ኳሶች እና ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ መኩራዎች ግብ ለማግኘት ቢጥሩም እምብዛም ከባድ የሚባል ሙከራ አላደረጉም ነበር።

በቅድሚያ የተወሰደባቸውን ብልጫ መቆጣጠር የቻሉት መከላከያዎች በደደቢት የሦስትዮሽ የኋላ መስመር ግራ እና ቀኝ ደጋግመው በመግባት የተሻለ ጫና ፈጥረው መዝለቅ ችለው ነበር። ዛሬ የአጥቂ አማካይነት ሚናን ተቀብሎ ወደ ሜዳ የገባው ቴዎድሮስ ታፈሰ እንቅስቃሴ ላይ በተመሰረተ ሁኔታም በሁለቱ ክንፎች በገቡባቸው ቅፅበቶች ያለቀላቸው የሚባሉ ዕድሎችን ፈጥረው ነበር። 21ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ በግራ በኩል ለፍቃዱ ዓለሙ ካሻገረው ኳስ ፍሬው ወደ ግብ ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት 28ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቴዎድሮስ በቀኝ በኩል ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ረሽድ ማታውሲ ይዞበታል። ጦሩ በእጅጉ ለጎል በቀረበበት የ33ኛ ደቂቃ አጋጣሚ ግን ፍቃዱ ዓለሙ ሳጥን ውስጥ ከቴዎድሮስ የደረሰውን ኳስ ከግቡ አፋፍ ላይ በማይታመን መልኩ አምክኖታል። እነዚህን ተደጋጋሚ ጥቃቶች መቋቋም የቻሉት ደደቢቶች በ45ኛው ደቂቃ በፍጥነቱ የባለሜዳዎቸን የተከላካይ ክፍል ሲያስጨንቅ የቆየው መድሀኔ ብርሀኔ ፉሰይኒ ኑሁ ከግራ መስመር ካሻገረለት ኳስ በግንባሩ በማስቆጠር ቡድኑ እየመራ እርፍት እንዲወጣ አስችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ፍፁም ገብረማርያም እና ተመስገን ገብረኪዳንን ቀይረው በማስገባት የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ቁጥር ወደ ሦስት ከፍ ያደረጉት መከላከያዎች ያላቸውን ኃይል በሙሉ በመጠቀም ወደ ፊት ገፍተው ተጫውተዋል። በቅብብሎች ወደ ጎል ከመድረስ ይልቅም ረዘም ያሉ ኳሶችን ደጋግመው መጣልን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል። በዚህም 59ኛው ደቂቃ ላይ ዓለምነህ ግርማ ከመሀል ሜዳ ያሻማውን ኳስ ፍቃዱ በግንባሩ ሞክሮ ማታውሲ እንደምንም ነበር ያወጣበት። ከተሻጋሪ ኳሶች በተጨማሪ ከሳጥን ውጪም አክርረው በመምታት ለማስቆጠር ይሞክሩ የነበሩት ባለሜዳዎቹ 64ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ መንገድ ከሳጥን ውጪ የሞከሩትን ኳስ ማታውሲ ሲተፋው አግኝቶ ፍሬው አሳልፎለት ፍፁም በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት በቀጠለባቸው ደቂቃዎች መከላከያዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ቶሎ ቶሎ ኳሶችን ወደ ፊት ሲያሻግሩ በራሳቸው ሜዳ ላይ መቅረትን ምርጫቸው ያደረጉት ደደቢቶችም ጥቃቱን እየተከላከሉ በረጅም ኳሶች ምላሽ ይሰጡ ነበር። የተዋጣላት ጥምረት የነበራቸው የደደቢት አጥቂዎች ፉሰይኒ እና መድሀኔ ከተከላካዮች ጀርባ የሚጣልላቸውን ኳሶች ይዘው ለመግባት ሲጥሩ በተደጋጋሚ ይታይ ነበር። የመከላከያ የኋላ መስመር ተሰላፊዎችም ከግባቸው በብዙው ርቀው ለመሀል ሜዳው ቀርበው የነበረ ሲሆን ኳሶችን በቶሎ በማራቅ ሲከላከሉ ቢቆዩም ሁለተኛ ግብ ማስተናገድ ግን አልቀረላቸውም። 75ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ከረጅም ርቀት የተጣለውን ኳስ ፉሰይኒ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ሲያሻግር ከአቤል ማሞ ያመለጠችውን ኳስ መድሀኔ አግኝቶ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። በተቀሩት ደቂቃዎች እንግዶቹ ውጤቱን አስጠብቀው ለመጣት ተጠንቅቀው ጨዋታውን ሲጨርሱ በበኃይሉ እና ፍፁም ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት መከላከያዎች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ለሽንፈት ተዳርገዋል። በመጨረሻ ደቂቃ አበበ ጥላሁን እና ኑሁ ፉሰይኒ በፈጠሩት ሰጣ ገባ የአሸብር ሰቦቃ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነውም ጨዋታው ተጠናቋል።

በውጤቱ ደደቢት የደረጃ ለውጥ ባያደርግም ከሽረ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ስድስት ዝቅ ማድረግ ሲችል መከላከያ በ13ኝነት የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተገኝቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡