አአ U-17 | ኢትዮጵያ ቡና ሲያሸንፍ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 6ኛ ሳምንት ሁለት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ ኢትዮጵያ ቡና ድል አስመዝጥቧል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።

04:00 በጃንሜዳ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክን ከአዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር አስተናግዶ 2-2 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክር በተስተናገደበት በዚህ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት አዳማዎች ሲሆኑ ጎሉንም ሙባረክ ሸምሱ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሯል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተሽለው በታዩበት እንቅስቃሴ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ምንተስኖት ዓለማየሁ ወደ ጎልነት በመቀየር አቻ ሲሆኑ ብዙም ሳይቆዩ ኤሌክትሪኮች በአንዋር ሙራድ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረው 2-1 መምራት ችለዋል።

አስቀድመው ጎል አስቆጥረው ተነቃቅተው የነበሩት አዳማዎች በተከታታይ ሁለት ጎል ቢቆጠርባቸውም ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ልማደኛው አጥቂ ፍራኦል ጫላ አስቆጥሮ አዳማን ሁለት አቻ ማድረግ ችሏል። ፍራኦል እስካሁን በውድድሩ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ወደ ዘጠኝ በማድረስ ኮከብ ጎል አስቆጣሪነቱን በብቸኝነት መምራት ችሏል። ከእረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ከሚደረጉ የጎል ሙከራዎች በቀር ሌሎች ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል።

06:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ሀሌታ መካከል በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ የሳምንቱን ምርጡን እንቅስቃሴ አስመልክቶን ኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸንፏል። ከወትሮ ብዛት ለው ተመልካች በተከታተለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የተመለከትነው አምራን ሱሌይማን ገና በጨዋታው የመጀመርያ አንድ ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ነበር ኢትዮጵያ ቡናዎች መምራት የጀመሩት። ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሀሌታዎች አቻ ለመሆን አርባ ሁለት ደቂቃ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸው ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ሻሂዱ ሙስጠፋ ባስቆጠራት ጎል አቻ ሆኑ።

በሁለተኛው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ፉክክር በብርቱ ቀጥሎ በሚገርም የአጨራረስ ብቃት ከርቀት አማካዩ አንዋር ሲራጅ ግሩም ሁለተኛ ጎል ለኢትዮጵያ ቡና አስቆጥሮ ቡናማዎቹ መምራት መምራት ችለዋል። ጎሉን ያስቆጠረው አንዋር ሲራጅ በተለያዩ የዙር ጨዋታዎች ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል መልካም እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሲሆን ለወደፊቱ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን መመልከት ችለናል። በቀሪው ደቂቃዎች ሀሌታዎች ጎል ለማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ ውጤት ለማስጠበቅ ያደረጉት ትንቅንቅ ቢቀጥልም በመጨረሻም በኢትዮጵያ ቡና 2-1 በሆነ አሸናፊነት ተፈፅሟል። ኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ አጀማመሩ ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም ከ5ኛው ሳምንት ጀምሮ ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች አከታትሎ በማሸነፉ ደረጃውን ሊያሻሽል ችሏል።

ለኢትዮ ኤሌትሪክ፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ዓመት በግብ ጠባቂነት ያገለገለው እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወንዶች እንዲሁምበአሁኑ ሰዓት የኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ የሚገኘው ፀጋዘዓብ አስገዶም ልጅ ሚሊዮን ፀጋዘዓብ በአማካይ ስፍራ ተጫዋችነት ሀሌታን እያገለገለ ይገኛል።

* በዳኝነት አመዳደብ በኩል የመጀመርያው ሳምንት ጨዋታዎች በኃላ እየተስተካከለ በጥሩ ሁኔታ ውድድሩ እየቀጠለ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቡናን ከሀሌታ የመሩት ዳኛ በሚወስኑት ያልተገባ ውሳኔ ምክንያት የጨዋታውን መንፈስ ከመረበሻቸው ባሻገር በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተቃውሞ ሲያስተናግዱ ውለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡