ከፍተኛ ሊግ ለ | መድን በመሪነቱ ሲቀጥል ወልቂጤ ወደ አሸናፊነት ተመለሷል


የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ሲደረጉ በሠንጠረዡ አናት ተከታትለው የተቀመጡት ሦስት ቡድኖች አሸንፈዋል።

በአዲስ አበባ መድን ሜዳ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ መድን እና ሀምበሪቾ ጨዋታ መድን 1-0 በማሸነፍ መሪነቱን አስጠብቋል። በነፋሻማ እና አልፎ አልፎ እያካፋ በተደረገው የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ የግብ አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። የሀምሪቾው ዘካርያስ ፍቅሬ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ መትቶ በግቡ አናት ላይ የወጣበትም የመጀመርያው ሙከራ ነበር። በኢትዮጵያ መድኖች በኩል ደግሞ በ10ኛው ደቂቃ ምስጋናው ወልደዮሀንስ ከተጋጣሚ ግብ ክልል በቅርብ ርቀት ያገኘውን የግብ አጋጣሚ አክርሮ መትቶ በግቡ ግራ አግዳሚ በኩል የወጣበት የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ነበር።

ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል የሚደርሱት ሀምበሪቾ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ አክርሮ ተመስገን አሰፋ አክርሮ ሞክሮ የግቡን የግራ አግዳሚ ታኮ ሲወጣበት በ22ኛው ደቂቃ ላይ አንጋፋው የፊት መስመር ተጫዋች በረከት አዲሱ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥቶበታል። ከነዚህ ሙከራዎች በኋላ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጽያ መድን አመራሮች ኳስ በሀምበሪቾ የግብ ክልል ውስጥ እጅ ተነክቶ በዝምታ ታልፈል፤ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር በሚል ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን ከዛ በመለስ የጨዋታ መንፈስ ከፍተኛ ውጥረት እንዲታይበት ምክንያት ሆኗል። ቀጥሎ ባሉት ደቂቃዎችም ሊጠቀስ የሚችል የጠራ የጎል እድል ሳይፈጠርበት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ኢትዮጵያ መድኖች ጫናቸውን በጎል አጅበዋል። በ49ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ምስጋናው ወልደ ዮሐንስ በግንባሩ በመግጨት የማሸነፊያውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ኋላ ያፈገፈጉት ባለሜዳዎቹ በርካታ የግብ ሙከራ አስተናግደዋል። በ51ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ኳስን በአግባቡ ተቆጣጥሮ በመቀስ ምት የመታው ኳስ በግቡ አናት ሲወጣበት ከ3 ደቂቃዎች ልዩነት በኋላ በረከት አዲሱ ላይ ጥፋት ተፈፅሟል በሚል ሀምበሪቾዎች የፍፁም ቅጣት ምት እድል ቢያገኙም አጥቂው ዘካርያስ ፍቅሬ መትቶ ግብ ጠባቂው ጆርጅ ደስታ መልሶበታል። የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ ያገኘው ዘካርያስ በግቡ አናት ወጥቶበታል። ከክስተቱ በኋላም መድኖች የተሠጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ትክክል አይደለም በማለት ክስ አስመዝገበዋል።

ባለሜዳዎቹ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት የሚደርጉት ጥረት ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጥ የነበረ ሲሆን ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ግን ተሳክቶላቸው ወጥቷል። እንግዳው ቡድን ውጤቱን ለመቀልበስ በተለይም በ63ኛው ደቂቃ ምኞት ማርቆስ መትቶ የግቧን አግዳሚ ለትማ የወጣችበት እንዲሁም ውንድሜነህ ዘሪሁን ያደረጉት የነበረው የግብ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

በዚሁ ምድብ በደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 3-2 አሸንፏል። ለወልቄጤ ከተማ አምበሉ ብስራት ገበየው፣ ሲሳይ ቶሌ (በፍፁም ቅጣት ምት) እንዲሁም የቀድሞ የሀምበሪቾ ተጫዋች ቢንያም ጌታቸው ሶስቱን ግቦች ያስቆጠሩ ናቸው። ለአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ማሀጅር መኪ (በፍፁም ቅጣት ምት) እና ዓላዛር ሁለቱን ግብ አስቆጥረዋል።

ቅዳሜ ድሬዳዋ ላይ ናሽናል ሴሜንትን የገጠመው ኢኮስኮ በአቤኔዘር አቴ በነኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ በፉክክሩ ቀጥሏል። ከጨዋታው በፊት የኢኮስኮ የቡድኑ አመራሮች ለሶከር ኢትዮጽያ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ” መጫዋቻ ሜዳ ድሬዳዋ ዋና ስታዲየም እንዲሁን ፕሪ-ማች ላይ ብናወራም ስታድየሙ ሌላ አገልግሎት ላይ መዋሉን ተገልፆልን የነበር ቢሆንም ሜዳው ድረስ ካለሄድን አናምንም በማለታችን ቦታ ድረስ ስንሄድ ምንም አይነት ነገር ባለመኖሩ ጨዋታው ዋና ስታዲዮም ላይ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር። ሆኖም የጨዋታው መዳረሻ ላይ ከፌዴሬሽን አካላት ተደውሎልኛል በማለት ሳቢያን ሜዳ ተጫዋቱ ተብለናል። እኛ አሁን የምንገኘው ዋናው ሜዳ ነው። ለሚመለከተው ሁሉ ብንደውል ምላሽ የሚሰጠን የለም። አንድ ወይም ሁለት ቡድኖችን ለመጥቀም ተብሎ እኛ መጎዳት የለብንም። ምንም ማድረግ ስለማንችል እዛ ድረስ ሄደን እንጫወታለን።” ሲሉ ከጨዋታው በፊት አስተያታቸውን ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ ቀን ቅዳሜ ጠዋት ላይ 4:00 ስዓት ላይ ድሬዳዋ ፖሊስ ከወላይታ ሶዶ ያደረጉት ጨዋታ በድሬዳዋ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቆል። ድሬዳዋ ፖሊስ 5 ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዘሪሁን፣ በ10 ኛው ደቂቃ አቤል ብርሃኑ፣ በ32ኛው አብዱልፈታ ከማል ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ለወላይታ ሶዶ ደግሞ 14ኛው ደቂቃ ላይ ሰለሞን ፋሲካ እና በ50 ኛው ደቂቃ በረከት ወንድሙ ያስቆጠሩ ናቸው። ከጨዋታው በኋላ የወላይታው ሶዶ አሰልጣኝ ጳውሎስ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ” እዚህ ሜዳ ላይ ተጫውቶ ማሸነፍ በፍፁም አይቻልም። ሜዳው አጥር የለውም። በዚህ ምክንያት ከጀርባ የምተሰማው ድምፅ በጣም የሚረብሽ ነው አወዳዳሪው አካል ሜዳውን መጥቶ ቢመለከተው። “በማለት መልክታቻውን አስተላልፈዋል።

ዲላ ላይ ዲላ ከተማ ከ ሀላባ ያደረጉት ጨዋታ በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ በቀረበው ዲላ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሄኖክ ተረፈ ብቸኛው የጎል ባለቤት ነው።

አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ የካ ክፍል ከተማን 2-0 አሸንፏል። በ62ኛው ደቂቃ ላይ ቴውድሮስ ታምሩ እና በ80 ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ቦጋለ ለነገሌ አርሲ ግቦችን አስቆጥረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡