” ኦሊምፒክ ቡድኑ ነገ ለምንገነባው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ግብዓት ነው” አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በማሊ በድምር ውጤት 5-1 ተሸንፎ ከ2020 የኦሊምፒክ ማጣርያ ከተሰናበተ በኋላ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ በተገኙበት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚዲያ ክፍል በተለይም ማሊ ላይ የተደረገው የመልስ ጨዋታ ላይ ያተኮረ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

አሰልጣኝ አብርሀም በቅድሚያ በሰጡት ማብራርያ የሜዳቸውን ውጤት አለማስጠበቃቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል። “በሜዳችን ጥሩ ነበርን፤ በጨዋታም እንቅስቃሴ በልጠን ነበር የተገኘነው። በመልሱ ጨዋታ ግን ያንን መድገም አልቻልንም። የኦሊምፒክ ቡድኑ ጥሩ ስብስብ ያለው እና ብዙ ተስፋ የሚጣልባቸው ነገሮች ያሳየን ነው። በዚህ ውድድር ላይ የተማርነው ነገር ቢኖር በሜዳችን ላይ ዕድላችንን በሙሉ መጠቀም መቻል እንዳለብን ነው። ትምህርት ሰጥቶን አልፏል።” ብለዋል።

በመቀጠል አልጣኙ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሾች ሰጥተዋል።

የብሔራዊ ቡድኑ ችግር ውጤት አስጠብቆ መውጣት ላይ ነው። በተለይ በመጨረሻው ደቂቃዎች ላይ ጎል እየተቆጠረብን ነው፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መተግበር ይኖርብናል። ተጫዋቾች ላይ ቀደም ብሎ በሚቆጠሩ ግቦች ላይ ያለው የሥነ-ልቦና ወይም የአዕምሮ ጥንካሬ ላይ መስራት አለብን። በመጨረሻው ደቂቃዎች ላይ ተጋጣሚ ቡድን የሚፈጥረውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል ቅርፅ መያዝ፣ በተለይም ወደፊት ተጭኖ በማጥቃት ተጋጣሚን ጫና መቀነስ ይቻላል።

የማሊው አሰልጣኝ አስተያየት በሚሰጥበት ወቅት ተጫዋቾቹ ላይ የሚፈጥረው ጫና ይኖራል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾቹ የዓለምአቀፍ ጨዋታዎች ልምድ አለመኖሩ ነው። ነገር ግን ይህን ለመቅረፍ እዚህ አዲስ አበባ ሳለን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የስፖርት ሥነ-ልቡና ባለሙያ በማምጣት አስተያየቱ በእኛ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳይችል ጥረት አድርገንበታል።

የጊዜ ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል። አንድ ቡድን ለመስራት ከ6-8 ሳምንት ያስፈልጋል። የሀገራችን የውድድር መርሃ ግብር ከዓለምአቀፍ ውድድር ጋር ባለመጣጣሙ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ በመፍጠሩ ይህን የግድ ማስተካከል ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ውድድር እንዳይቋረጥ በማሰብ ጭምር ከየቡድኖቹ ከሁለት በላይ ተጫዋቾች አልወሰድንም። ነገር ግን ከኢንተርናሽናል መርሃ ግብር ጋር አብሮ ቢሄድ እንደልብ መንቀሳቀስ እንችል ነበር። ይህን ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር በጋራ የምናስተካክለው ነው የሚሆነው። ጊዜው የምንፈልገውን መስራት አላስቻለንም፤ ይህን ወደ ፊት የምናሻሽለው ይሆናል።

ዳኝነቱ በተመለከተ እንደሰበብ እንዲቆጠርብኝ ወይም ሽፋን ማድረግ አልፈልግም። ምክንያቱም የራሳችንን ችግር መደበቂያ እንዳይመስል ነው። ነገር ግን ዳኝነቱ ላይ በደሉ በግልፅ የሚታይ ነበር። ከጨዋታው በፊት ባለው ፕሪ- ማች የካፍ የዳኞች አሰሰር አለመኖሩን በእለቱ ላለው ኮሚሽነር አሳውቀናል።

ይህን ቡድን እየሰራን ነው ያለነው በተለይ ወደፊት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን በይበልጥ እያገኘ ሲመጣ ጠንካራ እና አስተማማኝ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ነው። የኦሊምፒክ ቡድኑ የኢንተርናሽናል ልምድ እንዲያገኝ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ እየሰራንበት ነው። እዚህ ቡድን ውስጥ ወደፊት በዕድሜ ምክንያት ያልተካተቱት ተጫዋቾች በማካተት ለብሔራዊ ቡድኑ ተተኪ የሚሆን ቡድን (Shadow Team) የምንሰራ ነው የሚሆነው። ይህ ቡድን የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ያገኝ ዘንድ ሞሮኮ በነበረኝ ቆይታ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማግኘት ውይይት ያደረግን ሲሆን ይህን እድል በመጠቀም የበለጠ ልምዶችን ማግኘት የምንችልበትን ስራ እየሰራን ነው።

ውጫዊ ችግሮች ነበሩ ወይ? አዎ በጣም ነበሩ። እኛ የተነገረን አርቲፍሻል ሜዳ ላይ ጨዋታ እንደምናከናውን ነበር። ግን ልምምድ የሰጡን ሜዳ 41°c ላይ በሚገኝ አርቲፍሻል ሜዳ ላይ ነበር ። ዋናው ሜዳ በጣም አመቺ በተለይ እንደኛ ኳስን ይዞ ለመጫወት ምርጫው ያደረገ ቡድን የሚመርጠው ሜዳ ነበር። ግን እዛ እንድንጫወት ፍቃደኛ አልሆኑም። ከዚህ በተጨማሪ የጨዋታ ሰዓት ለውጥም አድርገውብናል። ከውስጣዊ ችግሮች አንዱ የሜዳው በስፋት መጠን ችግር ነው። የትም ስትሄድ ሙሉ መረጃ መውሰድ ለምትፈልገው አጨዋወት ይረዳህ ዘንድ ጥሩ ግብአት ነው። ነገር ግን እኛ የምናውቀው የነበረው ዋናው ሜዳ ላይ እንደምንጫወት ነበር። አርቴፊሻሉ ሜዳ በመጠን ከዋናው ሜዳ ያንሳል። ይህም ችግር ነበር።

ከሽንፈቱ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ጫና ውስጥ አይደለሁም። ለምን ጫና ውስጥ እሆናለው። ነገ ለምንገነባው ጠንካራ እና አስተማማኝ ብሔራዊ ቡድን ይህ በራሱ ጥሩ ግብዓት ነው። በይበልጥ ችግሮችን እያስወገድን ጠንካራውን ብሔራዊ ቡድን እንሰራለን።

አማኑኤል ዮሐንስ (አምበል)

አብዛኛውን ነገር ዋና አሰልጣኝ ተናግረውታል። በጨዋታው ላይ የሥነ-ልቡና ችግር ታይቶብናል። ምክንያቱ ደሞ በግልፅ ለሚታዩ ጥፋቶች ዳኛው ምንም ውሳኔ አይሰጥም። በተለይም አፈወርቅ ላይ የተሰራው ጥፋት ይታለፍ ነበር። ሜዳ ውስጥ የነበረው አየር ሙቀት ከበድ ይል ነበር። አሰልጣኙ የሚፈልገውን ነገር መተግበር አልቻልንም። ምክንያቱ ደሞ የነበረው ጫና ነው። ቡድኑ ጊዜ ከተሰጠው ጠንካራ ቡድን ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡