ሀዋሳ ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ስጥተዋል።
“ከሽንፈት እንደመምጣታችን በተጫዋቾቼ ላይ ጭንቀት ነበር” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው እንደተመለከታችሁት በጣም ጥሩ ነበር። ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ጀምሮ ተከታታይ ሶስት ጨዋታ ከሜዳችን ውጭ ነበር ያደረግነው። መልበሻ ክፍል የተነጋገርነው ጨዋታውን በማሸነፍ ከጭንቀት መውጣት እንዳለባቸው ነበር። አዳማ በጨዋታው በጣም ጥሩ ነበሩ። ነገር ግን ልጆቼ በነበራቸው የማሸነፍ ተነሳሽነት አሸንፈን ልንወጣ ችለናል። ግን ከሽንፈት እንደመምጣታችን በተጫዋቾቼ ላይ ጭንቀት ነበር።
በጊዜ ተጫዋች የመቀየራቸው ጠቀሜታ
ምንም ጥርጥር የለውም ጠቅሞናል። ቡድናችን አጥቅቶ እንዲጫወት በሶስት ተከላካይ ለመጫወት ነበር ያሰብነው። እነሱ መሀል ላይ በዛ ብለው በሶስት የተከላካይ አማካይ ሲጫወቱ ስለነበር ኳሶቻችን መሀል ላይ ሲበላሹብን ነበር። የነበረን ምርጫም ዳር እና ዳር ክፍት ስለነበር በዛ ለመጫወት አስበን ነው። ተስፉ ከጉዳቱ ባያገግምም ቀይረን አስገብተነው በዚህም ውጤታማ ሆነናል።
የዋንጫ ፉክክር
በፉክክር ውስጥ አለን፤ ይህ ግልፅ ነው። ዛሬም ብሸነፍ ኖሮ የምናገረው ይህን ነው። ምክንያቱም ቡድናችን ዋንጫ የማንሳት አቅም አለው። ስንሸነፍ በጥቃቅን ስህተቶች እንጂ ብልጫ ተወስዶብን አይደለም። አሁንም ተስፋው ስላለን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።
“ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት ይገባን ነበር” ሲሳይ አብርሀም – አዳማ ከተማ
ስለጨዋታው
በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር በመጀመሪያዎቹ ሰላሳ ደቂቃዎች ተጭነን ነበር የተጫወትነው። ያገኘናቸው እድሎችም መጠቀም አልቻልንም። ከሜዳችን ውጭ ስለተጫወትን ነጥብ ይዘን ለመመለስ ነበር ያሰብነው ተጫዋቾቼም ይህን ለማድረግ የተቻላቸውን አድርገዋል፤ ግን አልተሳካም። ቢሆንም ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት ይገባን ነበር።
በወጥነት አለመቀጠል
ይህ በእግር ኳስ ውስጥ የሚያጋጥም ነገር ነው። ዛሬ ስላሸነፍክ ነገ ታሸንፋለህ ማለት አይደለም። ግን ስታሸንፍ በተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረው ጥሩ መንፈስ አለ። እሱም ለቀጣይ ጨዋታ ስንቅ ይሆንሀል። በቀጣይ እናስተካክላለን አሁን ግን በቡድኔ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ።
በስተመጨረሻ መናገር የምፈልገው ነገር በጨዋታው የተቻላቸውን ሁሉ ያደረጉት ተጫዋቾቼ እና ቡድናችንን ለማበረታታት ብዙ ኪሎሜትር ተጉዘው የመጡትን ደጋፊዎች እንዲሁም ከጎኔ ሆነው የሚረዱኝን የአሰልጣኝ አባላት በጣም አመሰግናለው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡