ኢትዮጵያ ቡና እድሉ ደረጄን እና ደሳለኝ ግርማን ከኃላፊነት አነሳ

– ለፖፓዲች ማስጠንቀቅያ ተሰጥቷል

ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ የአሰልጣኝ ፖፓዲች ረዳት አድርጎ ሾሞት የነበረውን እድሉ ደረጄን ከኃላፊነት ሲያነሳ የቴክኒክ ዳይሬክተሩ ደሳለኝ ግርማንም አሰናብቷል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ድራጋን ፖፓዲችም ማስጠንቀቅያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አምበል እድሉ ከዋና አሰልጣኙ ጋር ተግባብቶ መስራት አልቻለም በሚል ከወናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ተነስቶ ከ20 አመት በታች ቡድኑን ሲረከብ ከ20 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ የነበረው ገዛኸኝ ከተማ የእድሉን ቦታ ተክቶ የፖፓዲች ረዳት እንደሚሆን ታውቋል፡፡

በክረምቱ የኢትዮጵያ ቡና ቴክኒክ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ደሳለኝ ግርማም የስንብት እጣ ደርሷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና አቶ ደሳለኝን ሲቀጥር የሴቶቹን ፣ የወጣት እና የዋናውን ቡድን እንቅስቃሴ እንዲመራ ቢሆንም ሙሉ ትኩረቱን በዋናው ቡድን ላይ ብቻ በማድረጉ በስምምነት ከሃላፊነት ተነስተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ቡና በሚፈልገው ውጤታማነት ላይ እንዲያተኩሩ ማስጠንቀቅያ እንደደረሳቸው ከክሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና አንዋር ያሲንን አሰናብቶ እድሉ ደረጄን በረዳት አሰልጣኝነት ከሾመ 4 ወር እንኳን አልሞላውም፡፡

 

ያጋሩ