የዛሬ አመሻሹን የቡና እና ፋሲል ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።
ከአርብ ጀምሮ ሰባት ጨዋታዎች የተስተናገዱበት የሊጉ 19ኛ ሳምንት ዛሬ በኢትዮጵያ ቡና እና ፋሲል ከነማ የ11፡00 ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል። በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ድል የቀናቸው ሁለቱ ክለቦች የላይኛው ክፍል ላይ ለውጦችን ሊያመጣ የሚችል ተጠባቂ ጨዋታ ነው የሚያደርጉት።
ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ በተስተካካይ ጨዋታ ደደቢትን ማሸነፍ የቻለው ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ነበር ያገገመው። ከዚህም በላይ ቡድኑ በመጀመሪያው ዙር ራሱ ደደቢትን 2-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጨዋታ ከአንድ በላይ ግብ አስቆጥሯል። ይህ በራሱ ቡና በቀሪ ጨዋታዎች ከግብ ፊት የሚገኙ ዕድሎችን ወደ ውጤት ለመቀየር በስነልቡናው በኩል መሻሻል እንዲያሳይ ሊያደርገው ይችላል። ዳግም ሦስት አጥቂዎችን መጠቀም የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና በዛሬው ጨዋታ መሀል ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ በመሞከር በተለይም ወደ በሁሴን ሻቫኒ በኩል ባደላ የመስመር ጥቃት የአፄዎቹን የኋላ መስመር ለማለፍ እንሰሚሞክር ይጠበቃል። ነገር ግን ቡድኑ ግብ ያማስቆጠር ግዴታ ውስጥ በሚገባባቸው ደቂቃዎች ከግብ ክልሉ ከሚርቀው የተከላካይ መስመሩ ጀርባ በሚኖረው ሰፊ ክፍተት በቀላሉ ለጥቃት ሲጋለጥ መታየቱ ዛሬም ሊቸገርበት የሚችለው ነጥብ ነው። ምንም የተለየ ጉዳት የሌለባቸው ቡናዎች እስካሁን ያላገገሙት ተመስገን ካስትሮ ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ኢስማ ዋቴንጋን ብቻ የሚያጡ ይሆናል።
በሁለተኛው ዙር በብዙ ተሻሽለው ከቀረቡ ቡድኖች መካከል ዋነኛው የሆነው ፋሲል ከነማ ከሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። በመሆኑም ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ማለት የቻለ ሲሆን የትናንቱን የሲዳማ ቡና ድል ተከትሎ ወደ 3ኛነት ቢወርድም ዛሬ ማሸነፍ ከቻለ ደረጃውን ዳግም መረከብ ይችላል። ሳምንት የመሪው መቐለን ያለመሸነፍ ጉዞ መግታት ያቻሉት አፄዎቹ ዛሬ የተለየ አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል። በመቐለው ጨዋታ የፊት መስመሩን የሦስትዬሽ የማጥቃት ጥምረታቸውን ቁጥር ሳይቀንሱ የኋላ መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ወደ ሦስት ዝቅ አድርገው ሙሉ ለሙሉ በማጥቃት ላይ ተመስርተው ወደ ሜዳ የገቡት ፋሲሎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ነበር ወደ ቀደመው ቅርፃቸው የተመለሱት። ሆኖም የዛሬው ጨዋታ ከሜዳ ውጪ እንደመደረጉ እና አማካይ ክፍል ላይ በቀላሉ የበላይነት ለመውሰድ ቀላል ስለማይሆን አፄዎቹ በ 4-3-3 አሰላለፍ እንደሚጠቀሙ ይገመታል። በመስመር አጥቂዎቻቸው ፍጥነት ላይ ተመስርተውም በቶሎ ወደ ማጥቃት በመሸጋገር የግብ ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል። የፊት መስመራቸውን የመምራቱን ኃላፊነት ለሙጂብ ቃሲም በመስጠት የቀጠሉት ፋሲሎች ከኤፍሬም አለሙ እና አብዱርሀማን ሙባረክ ጉዳት ውጪ ቀሪ የቡድን ስብስባቸው መልካም ጤንነት ላይ ይገኛል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ከ2009 የውድድር ዓመት ጀምሮ ክለቦቹ በተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች ተነጣጣኝ ውጤት አላቸው። በዚህም ሁለት ሁለት ጊዜ ሲሸናነፉ አንዴ ያለግብ ተለያይተዋል። ኢትዮጵያ ቡና ሰባት ፋሲል ከነማ ደግሞ አምስት ግቦችንም አስቆጥረዋል።
– አዲስ አበባ ላይ ባከናወኗቸው ሁለት ጨዋታዎች ፋሲል የ1-0 ቡና ደግሞ የ 3-2 ድሎችን አስመዝግበዋል።
– ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድየም 11 ጨዋታዎችን ያከናወኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች አምስቱን በድል ሲወጡ ሦስት የአቻ እና ሦስት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል።
– ከሜዳ ውጪ በአብዛኛው የአቻ ውጤት የሚቀናቸው ፋሲሎች ከጎንደር ወጥተው ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ሁለት ጊዜ ድል አድርገው በሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል።
ዳኛ
– በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተጠምዶ የቆየው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ጨዋታውን ለመምራት ተመድቧል። በአምላክ በሊጉ አዳማ ከጊዮርጊስ አባ ጅፋር ከወላይታ ድቻ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች የዳኘ ሲሆን ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-4-3)
ወንድወሰን አሸናፊ
ኃይሌ ገብረትንሳይ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን – አህመድ ረሺድ
ካሉሻ አልሀሰን – ሄኖክ ካሳሁን – አማኑኤል ዮሃንስ
ሁሴን ሻቫኒ – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰዒድ ሁሴን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን
ሠለሞን ሐብቴ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው
ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ