ከካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች መካከል የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላካን ከጊኒው ሆሮያ የፊታችን ቅዳሜ የሚያገናኘው ወሳኝ የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ዳኞች ይመሩታል።
የካፍ የ2019 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ አላፊ ስምንት ቡድኖች የመጀመርያ ጨዋታቸውን በሳምንቱ መጨረሻ ማድረጋቸው ይታወቃል። የመልሱ ጨዋታ ደግሞ የፊታችን ዓርብ እና ቅዳሜ በአራት ሀገሮች ይካሄዳል። ሞሮኮ ላይ በሚደረገው የዋይዳድ ካዛብላካ እና የሆሮያ ጨዋታም ከ15 ቀናት በፊት የካፍ ሱፐር ካፕን የመራውና ዛሬ የቡና እና ፋሲል ጨዋታን የዳኘው ዓለም አቀፍ ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት ሲመራው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ተመስገን ሳሙኤል እና ሁለት ኬንያዊ ዳኞች በረዳትነት የሚመሩ መሆናቸውን ካፍ አሳውቋል።
ካፍ አስቀድሞ በዓምላክ እና ተመስገንን መድቦ የነበረው የዲሞክራቲክ ኮንኮው ቲፒ ማዜምቤ እና የታንዛኒያው ሲምባ የመልስ ጨዋታ ቢሆንም በዛምቢያዊ ዳኛ ለውጦ ነው እነ በዓምላክን የሞሮኮውን ፍልሚያ እንዲመሩ የተደረገው። የታንዛኒያው ክለብ ሲምባ የዳኞቹ መቀየር ተገቢ አይደለም በማለት ለካፍ ቅሬታውን አሰምቷል።
ቅዳሜ ኮናክሪ ላይ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ያለ ጎል አቻ የተለያዩ ሲሆን ሆሮያ ጨዋታውን የዳኙት ጋቦናዊው ኤሪክ ኦቶጎ ሁለት ተገቢ የፍፁም ቅጣት ምቶችን ከልክለዋል በሚል ለካፍ ቅሬታውን በዛሬው ዕለት አሳውቋል።
የጊኒው ክለብ ሆሮያ ባሳለፍነው ወር የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስን መቅጠሩ የሚታወስ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡