በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 0ለ0 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ከእረፍት በፊት ሁለት ተጫዋቾች ተጎድተው ከሜዳ በመውጣታቸው በምንፈልገው መልኩ መንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡”- ገዛኸኝ ከተማ (ኢትዮጵያ ቡና)
ስለጨዋታው
“በሜዳው እንደተጫወተ ቡድን እንቅስቃሴያችን ጥሩ አልነበረም። ምክንያቱም በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ተጫዋቾች ተጎድተውብን ከሜዳ ወጥተዋል፤ በዚህም ይዘነው የገባነውን የጨዋታ እቅድ ለመቀየር በመገደዳችን የተነሳ በምንፈልገው መልኩ መንቀሳቀስ አልቻልንም፡፡”
ስለ ጨዋታ መደራረብ
“እኛ በዚህ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎችን አድርገናል። ይህ በራሱ የሚፈጥረው ጫና አለ። ነገር ግን በምክንያትነት ባይቀርብም ከዚህ በተሻለ በዛሬው ጨዋታ መንቀሳቀስ እንችል ነበር፡፡”
“ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁ በጣም አስገርሞኛል” – ውበቱ አባተ (ፋሲል ከነማ)
ስለጨዋታው
“የዙር ውድድር እንደመሆኑ በየትኛውም ጨዋታ ነጥብ ልትጥል ትችላለህ፡፡ ከሜዳ ውጪ እንደመጫወታችን ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ገምተን ነበር የመጣነው፤ እንደጠበቅነውም ፈታኝ ነበር፡፡ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ክፍት የሆነ ጨዋታ እንደነበር ይሰማኛል፤ እኛም የምንችለውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁ በጣም አስገርሞኛል። ምክንያቱም ጨዋታው ግቦች የሚቆጠሩበት ይመስል ነበር፤ ነገር ግን ማስቆጠር አልቻልንም። ነጥብ መጣላችን ለኛ መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም በእንቅስቃሴ ረገድ ብዙም መጥፎ ስላልነበርን በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ የምንችለውን ጥረት እናደርጋለን፡፡”
ስለ ዳኝነቱ
“ዓለምብርሃን የተጠለፈበት ኳስ ለእኔ ፍፁም ቅጣት ምት ይመስለኛል። ዳኛው የነበረበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበር፤ ምናልባት ትንሽ ቀረብ ባለ ቦታ ላይ ሆኖ ቢሆን ግን ለውሳኔም አይቸገርም ነበር፡፡ ከዛ ውጭ የጨዋታ ውጤቱን ሊቀይር የሚችል የጎላ ክስተት አልነበረም፤ በአጠቃላይ ዳኝነቱ ጥሩ ነበር፡፡”
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡