የሠላምና የወዳጅነት ውድድር አይካሄድም

በአራት ሀገሮች ተሳታፊነት በኤርትራ አዘጋጅነት ይካሄዳል የተባለው ውድድር እንደማይካሄድ ሲረጋገጥ ዝግጅቱን እያደረገ ለሚገኘው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምትኩ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርግ እንደሚችል ታውቋል።

“የሠላም እና የወዳጅነት” ጨዋታ ከሚያዚያ ሦስት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ኢትዮጵያ ፣ ጂቡቲ ፣ ሶማሊያ እና አዘጋጇ ሀገር ኤርትራ የሚሳተፉበት ውድድር እንደሚደረግ ቢነገርም አሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት ውድድሩ እንደተሰረዘ ሰምተናል። ለውድድሩ መቅረት ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን የተገለፀ ነገር የለም።

ይህን ተከትሎ ያለፉትን 15 ቀናት መቀመጫውን ሀራምቤ ሆቴል በማድረግ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ እየተመራ ዝግጅቱን በሚገባ እያካሄደ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ ውድድሩ መቅረቱን ተከትሎ ዝም ብሎ ቡድኑ ከሚበተን አንድ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ሰምተናል።

አዲስ አበባ እንደሚካሄድ በታሰበው በዚህ የወዳጅነት ጨዋታ ታጋጣሚዋ ሀገር ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች አንዷ የሀኘችው ጂቡቲ እንደምትሆን፤ ቀኑ እና ሰዓቱም ወደ ፊት እንደሚገለፅ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡