በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ አራት 4ኛ ክፍል እንዲህ ይቀርባል፡፡
|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ | LINK |
ፋሺስታዊ አገዛዝ የሰፈነባቸው የአውሮፓ ሃገራትም ጣልያን ከመረጠችው የእግርኳስ አቀራረብ ስልት ጋር የሚስተካከል መንገድ ተከተሉ፡፡ ልክ በሌሎች ቦታዎች እንደሆነው ሁሉ በስፔንም እግርኳስ በተመሳሳይ ሁኔታ ተጀመረ፡፡ እዚያም ጨዋታውን በማስተዋወቅ ረገድ ብሪታንያውያኑ ቀዳሚውን ድርሻ ወሰዱ፡፡
በደቡባዊ ምዕራብ የስፔን ክልል <ሚናስ ደ ሪዮ ቲንቶ> በተባለው የማዕድን ቁፋሮ ቦታ ላይ በሰፈሩ የሰራተኛው መደብ አባላት አማካኝነት የጨዋታው ተዘውታሪነት ስር እየሰደደ ሄደ፡፡ በ1973 እዚሁ አካባቢ ሂዩጅ ማትሰን የተባለ ብሪታኒያዊ ባለሃብት በወቅቱ ሊጠፋ የተቃረበ የመዳብ ማዕድን መፈለጊያ የቁፋሮና ማምረቻ መሬት ሊገዛ ወሰነ፡፡ የቦታው መግዣ ዋጋም ወደ 3.5 ሚሊየን ፓውንድ ተተመነ፡፡ የመጀመሪያው ክፍያ ከወርቅ በተሰሩ ሳንቲሞች እንዲፈጸም ስምምነት ላይ ተደረሰና ፍራንኮቹ በባቡር እና በተኮላሸ በሬ በሚጎተት ጋሪ ተጭኖ ተጓጓዘ፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሲታሰብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚወገዝ ድርጊት ቢሆንም በ1887 አንድም ስፔናዊ ተጫዋች ሳያካትቱ በቀረቡ ሁለት ቡድኖች መካከል የተካሄደው ግጥሚያ በሃገሪቱ እግርኳስ ታሪክ የተመዘገበ የመጀመሪያ ጨዋታ ሆነና የሳን- ሮክዌ ክልልን የደስታ ቀን አስጀመረ፡፡ በስፔናውያኑ ነባር ባህል ዋነኛውና ተመራጩ የመዝናኛ መስክ ከኮርማ ጋር የሚደረገው ፍልሚያ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ የተጠቀሰው ግጥሚያ ከመካሄዱ ከሶስት ዓመት ቀደም ብሎ በአካባቢው የመጠጥ ቤቶች እየተስፋፉ ሲሄዱ ሴተኛ አዳሪነት እየተለመደ በመምጣቱ ሳቢያ የማዕድን ቁፋሮ ላይ የተሰማራው ድርጅት ባህላዊው ጉሽሚያ ለሚዘወተርባቸው ቦታዎች ፍቃድ መስጠት አቆመ፡፡ በወቅቱ በብሪታኒያና ስፔን መካከል የሚከናወኑ ግጥሚያዎች ሁለቱ ሃገራት የሚወዳጁበት፣ የአጨዋወት መቀራረብን የሚፈጥሩበት እና ስፖርታዊ መስተጋብሮች የሚመሰርቱባቸውን ውድድሮች ለማሳደግ ትልም ያላቸው ስለመሆኑ አፈታሪኮች ያወሳሉ፡፡
ታዋቂው ጋዜጠኛ ጂሚ ባርንስ ግን ይህ ከእውነታ የራቀ አመክንዮ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ እንዲያውም ጨዋታዎቹ በስፔንና ብሪታንያ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ቁልጭ አድርገው ስለማሳየታቸው ያብራራል፡፡ ” ስፔኖቹ በሃገራቸው እንደራሳቸው ስፖርት የሚቆጥሩትና እጅጉን የሚዝናኑበት ፍልሚያ በጥበባዊ ፈጠራና ጀብዱ የታጀበ በመሆኑ ይህን መሰረታዊ መስፈርት በማያሟላው አዲሱ ጨዋታ እንደማይደመሙ ገና ከጅምሩ ግልጽ ነበር፡፡” ሲል የስፔንን እግርኳስ ጓዳ ጎድጓዳ ጠንቅቆ የሚያውቀው ባርንስ ገልጿል፡፡ እንግዲህ ከዚያ በኋላ ነው በስፔን ከኮርማዎች ጋር ፍልሚያ የመግጠም ባህላዊ ስፖርት እና የእግርኳስ ታሪኮች መወሳሰብ የጀመሩት፡፡
ብሪታንያውያን በቢልባኦ የማዕድን ማውጣት ዘርፍ ላይ በሰፊው በመሰማራታቸው በከተማዋ ልዩ ትኩረት ሊያገኝ የቻለው እግር ኳስ ቀስ በቀስም ሰፊ ተቀባይነት እየተቸረው መጣ፡፡ በ1913 በቢልባኦ የተገነባው ሳን-ማሜስ በስፔን የእግርኳስ ጨዋታ ብቻ እንዲካሄድበት ተብሎ የተወሰነለት የመጀመሪያው ስታዲየም ነበር፡፡ ይህም ውሳኔ የከተማይቱን ብሎም የሃገሪቱን እግርኳስ ውልደት አበሰረ፡፡ እንዲያም ሆኖ ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ያሳዩ የነበረው ጉልበተኛ ባህሪ ከብሪታንያውያኑ አቻዎቻቸው አጨዋወት በቀጥታ የተቀዳ ሆኖ ተገኘ፡፡
በስፔን እግርኳስ የጅማሮ ዓመታት የሃያልነቱን መንበር የተቆናጠጠው አትሌቲክ ክለብ ቀደም ሲል የተቋቋሙ ሁለት ቡድኖችን በማዋሃድ በ1903 ተመሰረተ፡፡ ከመስራቾቹ አንደኛው ቡድን በከተማዋ ይኖሩ ከነበሩ እንግሊዛውያን ሰራተኞች የተገኘ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሃገረ እንግሊዝ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ እግርኳሳዊ ግንዛቤ ያዳበሩት የ<ጂምናዚየም- ዛማኮይስ> ተማሪዎች ስብስብ ነበር፡፡
ከሁሉ የሚያስገርመው ደግሞ የአትሌቲክ ክለብ የመጀመሪያ አሰልጣኝ የብሪታንያ እግርኳስ ተጽዕኖ የተጸናወተው እንግሊዛዊው ሼፈርድ ሆኖ መሾሙ ነበር፡፡ ምንም እንኳ አሰልጣኙ ከባስክ ግዛት የሚመጡ ተጫዋቾችን ብቻ ለቡድኑ እንዲጫወቱ የሚፈቅድ ህግ አውጥቶ ወዲያው ተግባራዊ ማድረግ ቢጀምርም ክለቡ ግን ከእንግሊዝ ጋር የመሰረተውን ቁርኝት ይዞ ቀጠለ፡፡
አትሌቲክ ቢልባኦ በገንዘብ ረገድ በ<ዴ-ላ ሶታ> ኢንዱስትሪ እና የመርከብ አገልግሎት ደርጅት እገዛ ይደረግለት ነበር፡፡ ይህ ኩባንያ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የህብረቱ አባል ሃገራትን በተለይም ታላቋ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ሩሲያን ሲረዳ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወቅቱን የአለም ፖለቲካዊ ቀውስ ተቋቁሞ ከእነዚህ ሃገራት ጋር የንግድ ግንኙነቱን አስቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ክለቡ የእንግሊዞች ድምጸት የያዘውን ስያሜ እንዲሁም እንግሊዛውያን አሰልጣኞችን የመቅጠር ፖሊሲውን ተያያዘው፡፡
በ1914 አትሌቲክ ቢልባኦ ሼፈርድን በቢሊ ባርነስ ተካው፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ በ1902 ሼፊልድ ዩናይትድ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋንጫን ሲያነሳ በመልሱ ጨዋታ የማሸነፊያዋን ግብ ያገባና ቀደም ብሎ ለዌስትሃም፣ ሉተን እና ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ ተጫውቶ ያሳለፈ ነበር፡፡ ባርነስ በአትሌቲክ ቆይታው ሁለት የንጉስ ዋንጫዎችን ካሳካ በኋላ ወደ ብሪታኒያ ሄዶ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሃገራዊ ግዴታውን ከተወጣ በኋላ በነሐሴ 1920 ወደ ቢልባኦ ተመለሰ፡፡
” ሃገሪቷን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ የባስክ እግርኳስ አመርቂ እመርታ አሳይቷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እዚህ ስመጣ እግርኳሱ ዝግ ያለ፣ አጫጭር ቅብብሎች የሚበዙበት፣ ለዓይን የሚስብ ነገር ግን ፍጹም ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች የሆነና በስኮትላንዶች ዘይቤ የተቃኘ አጨዋወት ይዘወተር ነበር፡፡ እኔ በክለቡ ፈጣን፣ ረጃጅም ቅብብሎች ላይ ያመዘነ፣ በሜዳው ስፋት ወደ ግራና ቀኝ መስመሮች የሚላኩ ተሻጋሪ ኳሶችን የያዘ አቀራረብን አስተዋወቅሁ፤ መሃል ሜዳው ላይ ደግሞ ጎሎች የሚያስቆጥሩ ፈጣን ተጫዋቾችን ማሰለፍ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ አብዛኞቹ ክለቦች ይህን ዓይነት አጨዋወት ሲተገብሩ አስተውያለሁ፥ በአንጻሩ አትሌቲክ ያ መንገድ የጠፋው ይመስላል፡፡” ሲል ባርነስ ተናገረ፡፡
በ1920 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተካሄዱበት ወር የአትሌቲኮቹ ኃይልና ጉልበት የተቀላቀለበት አቀራረብ የስፔኖቹ አጨዋወት ስልት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ስፔን ብዙም የተጠባቂነት ጫና ሳትሸከምና ከሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል የተሰባሰቡ ተጫዋቾችን ይዛ ወደ ባተሌዋ የወደብ ከተማ አንትወርፕ አቀናች፡፡ በዚህኛው ክልል የሚገኙ ተጫዋቾች በሳር ላይ የመጫወት ልምድ ያዳበሩ ሲሆን በመሃለኛውና ደቡባዊ የሃገሪቱ ስፍራዎች ግን ፍርክስክስ ባለ ደረቅ የጭቃ ሜዳ ነበር የሚጫወቱት፡፡ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ስፓኒያርዶቹ ዴንማርክን 1-0 ረቱ፤ ይሁን እንጂ በሩብ ፍጻሜው የውድድሩን ወርቅ ሜዳይ አሸናፊ ቤልጂየምን ገጥመው 1-3 ተሸነፉ፡፡ በእርግጥ ሽንፈቱ በቶርናመንቱ የነበራቸውን ቆይታ የመጨረሻ አላደረገውም፤ ብሪታኒያዊው ዳኛ የፍጻሜውን ጨዋታ በመራበት መንገድ ደስተኞች ያልነበሩት ቼኮስሎቫኪያዎች ሜዳ ላይ በፈጠሩት ነውጥ ሳቢያ ከውድድሩ ሲታገዱ ስፔናውያኑ ቀደም ሲል በሰበሰቡት ነጥብ ታግዘው ወሰብሰብ ያለ ይዘት ባለውና የብር ሜዳሊያውን ለመውሰድ በሚደረግ ፉክክር ውስጥ ገቡ፡፡
ከዚያም የሁለተኝነቱን ስፍራ ለመቆናጠጥና ከኔዘርላንዶች ጋር ተፋልሞ የብር ሜዳዩን ለማሸነፍ ቀድመው ሲውዲንን 2-1፣ ቀጠሉና ጣልያንን 2-0 ረቱ፡፡ ሃገሪቱ በጥሎማለፉ የ3-1 ድል ስትቀዳጅ ፌሊክስ ሴሱማጋ ሁለት ግቦችን ከመረብ ጋር አዋሃደ፤ እንግዲህ ይህም ተጫዋች ከባስክ ግዛት ተገኝቶ የስፓኒያርዶቹ ጀግና የሆነ ነው፡፡ ከሲውዲን ጋር በተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ስፔን 0-1 ተመራች፤ ከእረፍት መልስ በስድስተኛው ደቂቃ ሆዜ ማሪያ ባላዉዜ አቻ አደረጋቸው፡፡ ተጫዋቹ በተደጋጋሚ በሚደርሱበት ግጭቶች የአፍንጫ ስብራት ገጥሞታል፤ በጅምር ያለውን የጸጉር መመለጥ ለመደበቅ ሲል አናቱ ላይ የሚያስረው መሃረብ መሳይ ጨርቅም ያበጡት ጆሮዎቹን ሸብበውለት ጉስቁል ያለ መልክ አላብሶታል፡፡ ከሁለተኛው ጎል መቆጠር ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዶሚኒኮ አሴዶ ማሸነፊያዋን ግብ ቢያክልም ለስፔናውያኑ መነሳሳትን የፈጠረችው የባላውዜ ቀዳሚ ግብ ነበረች፡፡ አጠቃላይ በጨዋታው የታየው ገጽታ በባስኮች ስልት የተቃኘ
ነበር፡፡ ማኖሎ ዲ ካስትሮ <ሃንዲካፕ> የሚል የብዕር ስም ተጠቅሞ እንደጻፈው “ጨዋታው ከእረፍት መልስ ሲጀምር ስፔኖች ከኋላ ተነስተው ለመፋለም እና ከፍተኛ የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ባደረጉት ትግል በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ከተጋጣሚ ግብ ክልል አቅራቢያ ቅጣት ምት እንዲያገኙ አገዛቸው፡፡” ይላል፡፡ በቀላሉ ሸረፍ ተደርጋ ወደ እርሱ የተሻገረችውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በመቀበል ከብዙ የተጋጣሚ ተጫዋቾች መሃል አፈትልኮ በመውጣት ኳስና መረብ አገናኘ፡፡ ሃንዲኬፕ ስለዚህች ጎል ምስክርነቱን ሲሰጥ
” ከፍተኛ ጥረትና ላቅ ያለ ብቃትን የምትጠይቅ ግብ!” ሲል ያወድሳታል፡፡ በማግስቱ የደች ጋዜጣ የስፔኖቹን የአጨዋወት ዘይቤ በ1576 አንትወርፕን ካወደሟት የሃገሪቱ ወታደሮች ተጋዳይነት ጋር አነጻጽሮ ለእግርኳስ አቀራረባቸው <ላ-ፉሪያ> የሚል ስያሜ ሰጣቸው፤ ስፔኖቹም ደስ ብሏቸው መጠሪያውን ተቀበሉት፡፡
ያቺ ጎል የ<ላ ፉሪያ>ን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ተግባር የቀየረ ትልቅ ታሪካዊ ትዕንግርት እንዲኖራት ተደረገች፤ በጊዜው ስለ ጎሏ አገባብ ሒደት በሃገሪቱ እጅግ ተጋኖ ተወራ፡፡ ታላቁ ግብ ጠባቂ ሪካርዶ ዛሞራ ባላውዜ ኳሷን በደረቱ አብርዶ ወደ ጎል ከመስደዱ በፊት መለያውን አጥብቀው የያዙትን አራት ሲውድናውያን ተጫዋቾች ደረማምሶ ማለፍ እንደተጠበቀበት ይገልጻል፡፡ ስለዚህም ስፔናውያኑ ትክክለኛው የአጨዋወት መንገድ የእነርሱ <ላ ፉሪያ> ዘዴ እንደሆነ ተረዱ፤ በስልቱ ላይም ከፍተኛ ዕምነት አሳደሩ፡፡ ባርነስ ይህን የጨዋታ አቀራረብ ሲተነትን ” ላ-ፉሪያ በተለየ ሁኔታ ጉልበትና ጀብደኝነት የሚያይልበት የእግርኳስ ዘይቤ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተጫዋቾች ዘንድ ይህን አጨዋወት ተግባር ላይ ለማዋል ውስጣዊ ፍላጎትና ከፍተኛ ቁርጠኝነት ይስተዋላል፡፡ ቀደም ሲል ባስኮቹ በክለብ ጀረጃ ሲጠቀሙበት እንደነበረና ስፔኖች የኮረጁት እንደሆነ ቅሬታ ቢያቀርቡም የጨዋታ አቀራረቡ በሃገሪቱ በሰፊው ተደራሽነቱ ሰፍቶ ብሔራዊ ማንነት እስከመሆን ደርሷል፡፡” ይላል፡፡
<ላ-ፉሪያ> የጨዋታ ስልት ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት ሲጀምር እንከኖቹም አብረው እየተጋለጡ ሄዱ፡፡ በሰኔ 1921 ባላውዜን ጨምሮ በርካታ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ያካተተው የባስኩ ክለብ በደቡብ አሜሪካ ሃገራት ግጥሚያዎችን የማካሄድ ጉዞ ወጠነና በመጀመሪያ ወደ አርጀንቲና አቀና፡፡ እዚያ የጠራ፣ ጥልቅ ውህደት የተላበሰና እጅጉን ቴክኒካዊ የበላይነት ላይ አተኩሮ የሚጫወተውን ተጋጣሚ ኳስ ለማስጣል ተቸግሮ ታየ፤ በግጥሚያው የቡዌኖስ አይረስ ምርጥ አስራ አንድ 4-0 ረታ፡፡ የስፔኑ ቡድን ቀጠለና ወደ ሮዛሪዮ፣ ሞንቴቪዲዮና ሳዖፖሎ አመራ፤ በየቦታው ይበልጡን ከእነርሱ የተሻሉ ባለክህሎት ባላንጦችን ገጥመው ከፍተኛ ብልጫ ተወሰደባቸው፤ በጉዞዎቹ ካካሄዷቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት ብቻ አሸንፈው፥ አንድ አቻ ተለያይተውና አምስት ደግሞ ተሸንፈው ተመለሱ፡፡
የዚያን ሰሞን ቢልባኦን የለውጥ ማዕበል አንዣበበባት፤ ሁኔታዎች ከቀድሞ ይዘታቸው ለየት ብለው መታየት ጀመሩ፡፡ ባርነስ በአትሌቲክ አንድ አመት ብቻ እንደሚከርም አሳወቀ፤ በቆይታውም ሌላ የንጉስ ዋንጫ አሸነፈና ቡድኑን ተሰናበተ፡፡ አትሌቲክም <ዴይሊ ሜይል> እና <ስፖርቲንግ ላይፍ> የተሰኙ ጋዜጦች ላይ ለአሰልጣኙ ምትክ እንደሚፈልግ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ጉጉ አመልካቾች መካከል ሚስተር በርተን ተመረጠ፡፡ በርተን በስራው ላይ ሁለት ወራትን እንዳስቆጠረ ሳምባዎቹ በጦርነቱ ወቅት በተመረዘ ጋዝ ተጠቅተው ደከሙና ጤናው ታወከ፡፡ ሁለት የቀድሞ ተጫዋቾች እና የቡድኑ አምበል በጋራ ሆነው ለጥቂት ጊዜያት ክለቡን መሩ፡፡ በመጨረሻ በሁለቱ የአለም ጦርነቶች መካከል በስፔን ከሰሩ ሁሉም ብሪታኒያዊ አሰልጣኞች በተለየ እጅግ የተከበረው አሰልጣኝ ፍሬድ ፔንትላንድ ቡድኑን ከአደጋ ታደገው፡፡
የበርሚንግሃም ከተማ ከንቲባ ልጅ የሆነው
ፔንትላንድ በብላክበርን፣ ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስና ሚድልስብራ ክለቦች ውስጥ በቀኝ መስመር አማካይነት ተጫውቶ አሳልፏል፤ ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንም አምስት ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ጂሚ ሆጋን ኦስትሪያን ለማሰልጠን ሲስማማ ትቶት የሄደውን ክፍት ቦታ ለመሸፈን ጀርመንን እንዲያሰልጥን የቀረበለትን ግብዣ ለመቀበል ወደ ሃገሪቱ አመራ፡፡ አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ከምዕራብ በርሊን አስር ኪሎሜትሮች ያህል ርቆ በሚገኝ <ረኸልበን> በተባለ የጦር ካምፕ ውስጥ በተዘጋጀ የእስረኞች ማጎሪያ ታሰረ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የማሰሪያ ቤቱ የሰዎች አያያዝ አሰቃቂ ነበር፡፡ እስረኞች በተባይ በተወረረ ሰሌን ላይ እንዲተኙ ፣ በአንድ የእጅ ቧንቧ እንዲታጠቡ፣ ተረከዙ ከእንጨት የተሰራ ጫማ እንዲጫሙ እንዲሁም ከከተሜው በጎ አድራጊዎች የሚለገሱ ኮቶችን እንዲለብሱ ተገደዱ፡፡ አንድ ጭልፋ ቀጭን ገንፎና በጣም የሚያቃጥል ትንሽ የቲማቲም ስልስ የእስረኞቹ ዕለታዊ ምግብ ነበር፡፡
ቀስበቀስ የጀርመን ባለስልጣናት እስረኞች
የራሳቸውን ጉዳይ እንዲከውኑ ፍቃዱ ሰጡ፡፡ ባርኒ ሮናይ በ<ኢሹ ስሪ ኦፍ ዘ ቢሊዛርድ> ላይ እንዳስቀመጠው ቀጥሎ የተከሰተው “ብሪታኒያውያን ራሳቸውን ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመታደግ ላሳዩት የጋራ ቁርጠኝነት እንዲሁም በሃገሪቱ ስር የሰደደ የተጠራጣሪነት ኗሪ ታሪክ ውስጥ ዘወትር በቸልታ የሚታለፈውን የተለያዩ ሐሳቦችን አልያም ዘዴዎችን በጥልቀት የማጤንና የሚበጀውን በመምረጥና በመወሰን ሒደት ውስጥ የሚታይ ፈጠራን የሚያካትት ባህላዊ የአገላለጽ መንገድን ማወደስ ነው፡፡” ይለናል፡፡ የፖስታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ የፓሊስ ሃይል ማደራጃዎች፣ ቤተ መጻህፍትና መጽሄት ማተሚያዎች ሲቋቋሙ አጠቃላይ ታሳሪው ማህበረሰባዊ እመርታዎችን አሳየ፡፡ የሜዳ ቴኒስ መጫወቻ ስፍራ፣ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር ቢሮ፣ ውርርድ ማዘውተሪያዎች፣ የፖስታ ማመላለስ አገልግሎት መስጫዎች፣ ሻይ ቤቶች፣ ለጽህፈት ቤትነት የሚያገለግሉ መለስተኛ ህንጻዎች እና ሁለት ደረጃቸውን የጠበቁ ሰፋፊ የእግርኳስ ሜዳዎች በካምፑ ካርታ የግንባታ ውቅር አውታር ንድፍ ላይ ተካተቱ፡፡
በወቅቱ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ወንዶች ቢሆኑም በሚገርም ሁኔታ እስር ቤቱ ውስጥ የታላቅ ስብዕናና ማንነት ስብጥር ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ ” ከቄንጠኛ ቤቶችም ሆነ ከጭርንቁስ መንደሮች ለተሰባሰቡ ግዞተኞች የስራ ክፍፍል አልያም የመደብ ልዩነት ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ሁሉም ታሳሪዎች በትንሿ የጓሮ ክፍል አንድ ላይ ታጭቀው ይታጎራሉ፡፡ የታላላቅ ኩባንያ ስራ አስኪያጆችና መርከበኞች፣ የሙዚቃ ትርዒተኞችና የፋብሪካ ሰራተኞች፣ የሳይንስ ልሂቃንና ፈረሰኞች ሌሎችንም ጨምሮ…..ሁላችንም በዚያ እስር ቤት ውስጥ ቅይጥ ህብረተሰባዊ መስተጋብር ፈጠርን፡፡ወደ ማብሰያ ቤት ሳመራ እንኳ በምዕራባዊ አውስትራሊያ የአንድ ከተማ ከበርቴ፣የእሳት አደጋ ሰራተኛ አልያም የኔ ቢጤ የሆነ ተራ ሰው ሊገጥመኝ ይችላል፡፡” ሲል አንድ የቀድሞ ታሳሪ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ባወጣው አነስተኛ የመጽሐፍ እትሙ አስነብቧል፡፡
አሰቃቂው ወህኒ ቤት በታዋቂና ግዙፍ ስብዕናን በተላበሱ ሰዎች ተጥለቀለቀ፡፡ በታላቁ ጉስታቭ ማኽለር ስር የሰለጠነው ስመጥሩ የክላሲካል ሙዚቃ መሪ ቻርለስ አድለር፣ ስለ ኑክሊየር ቦምብ ቀድሞ ሃሳብ ያመነጨውና በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ያሸናፈው ሰር ጄምስ ቻድዊክ፣ ምናልባትም በዚያን ወቅት በጣት ከሚቆጠሩ ጥቁር እንግሊዛውያኖች መካከል እየተከፈለው የፈረስ ውድድሮች ላይ ትንበያ የሚሰጠው ዝነኛው ፕሪንስ ሞኑሉሉ፣ ዘወትር ጫፉ ሰፋ የሚል ባርኔጣ ከአናቱ ጣል አድርጎ ፈገግ ሲል የሚታየው የአልኮል ሱስ ተጠቂውና የ<አይሪሽ ታይምስ> አርታኢ ‘ቤርቲ’ ስማይሊ፣ ( ጋዜጠኛው ከበረዶ ግግር የሚሰራ፣ አውሮፕላኖችን ሊያሳርፍ የሚችልና ለጥ ያለ ትልቅ ወለል ያለው ግዙፍ የጦር መርከብ የመገንባት ውጥን ሐሳብን ወደ ተግባር የቀየረ መምህርም ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ለወቅቱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል በቤታቸው የመታጠቢያ ክፍል በሚገኝ ገንዳ ውስጥ ሃሳቡን በናሙና ሊያሳያቸው ችሏል፡፡)
እንደ ፔንትላንድ ሁሉ ሌሎች ቁጥራቸው በርከት ያሉ የጊዜውና የቀድሞ ተጫዋቾች በወህኒ ቤቱ የተለያዩ ክፍሎች ተሰግስገዋል፡፡ የቀድሞው የሚድልስብራ የቡድን አጋሩ ስቲቭ ብሉመርም ከፔንትላንድ ጋር ታስሯል፡፡ ተጫዋቹ ለእንግሊዝ ባደረጋቸው ሃያሶስት ጨዋታዎች ሃያስምንት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ከዚያ በኋላ በሃምሌ ወር 1914 የ<ብሪታንያ በርሊን 92> ክለብ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ በ1914 የጸደይ ወቅት የሰሜን ጀርመን እግርኳስ ማህበርን የሚወክል ቡድን ለማሰልጠን የተስማማውና በብላክበርን አብሮት የተጫወተው የመስመር ተከላካይ ጓደኛው ሳም ዌልስተንሆልምም እዚያው ነበር፡፡ በሲውዲን፣ ሜክሲኮና ጀርመን ብሄራዊ ቡድኖች የአሰልጣኝነት ቆይታው ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈው የቀድሞው የሼፊልድ ዌንስዴይ የግራ መስመር አጥቂ ፍሬድ ስፓይክስሊ ከታሳሪዎቹ አንዱ ሆኗል፡፡ በቀድሞው ስኮትላንድን ብሄራዊ ቡድን የተጫዋችነት ዘመኑ ዝነኛ የነበረውና ቶተንሃምን ለማሰልጠን የቻለው ጆን ካሜሩንም ያንን ፍዳ ተጋርቷል፡፡ ለእስር በተዳረገበት ወቅት የጀርመኑን ድሬስደን ክለብ በማሰልጠን ላይ ይገኝ ነበር፡፡ በካሜሩን የአሰልጣኝነት ዘመን በቶተንሃም ክለብ ተጫውቶ <ቪክቶሪያ 89 በርሊን>ን ያሰለጠነው ጆን ብሬርሊም ከእነዚሁ ጓደኞቹ ጋር እስር ቤቱ ውስጥ ተገናኘ፡፡ ቤተሰቦቹ ከደቡብ ሺልድ ወደ ጀርመን ተሰደው ለሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ኤድዊን ደተንም የፔንትላንድ እስር ክፍል ተጋሪ ሆነ፡፡
እስረኞቹ ከተለመደው የህይወት ጫና ውጪ ሆነው አኗኗራቸውን ማሻሻልና በተሻለ ዘና የማለት መንፈስ ፈጠሩ፡፡ “የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፤ መጠነኛ መሻሻሎችም ታዩ፤ በንዑስ በንዑስ ተከፋፍለን የሩህልበን ታሳሪዎች ካምፕ ውስጥ የራሳችንን ዓለም ፈጠርን፡፡ አካል ብቃታችንን መጠበቅ ነበረብን፤ ለመንቀሳቀስና ለመለወጥ ፍላጎት ከማጣትና በሁኔታዎች ከመሰላቸት ራሳችንን መከላከልም ይገባን ነበር፡፡” ሲል ሌላው ታዋቂ ጋዜጠኛ ኢዝራኤል ኮኽን ፅፏል፡፡ በእስር ቤቱ በካልኩለስ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሒሳብ ፣ መለስተኛ ፊዚክስ ፣ ኦርጋኒክ እና ኢን-ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ፣ ራዲዮአክቲቪቲ (በጨረር ኃይል የሚመነጩ ንጥረነገሮች ላይ የሚያተኩር የትምህርት ዘርፍ)፣ ኼሬዲቲ (የስነ ባህሪ ውርስ ጥናት)፣ ባዮሎጂ ፣ በጀርመንኛ ቋንቋ የሚሰጥ የጀርመን ስነጽሁፍ፣ በጣልያንኛ ቋንቋ የሚሰጥ የጣልያኖች ስነጽሁፍ፣ የሼክስፒር ድርሰቶችን የሚመለከት እንዲሁም የኢውሪፒደስ (በጥንታዊ ግሪክ የትራጃይ ድራማ ዘውግ) ትምህርቶች ይሰጡ ነበር፡፡ ሙሉ የሙዚቃ ቡድን ያካተተ ቴአትር ቤትም ተቋቋመልን፡፡ የአዳራሹ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይም የሌሎች ሰዎችን ድርጊቶችና ድምጽ የሚያስመስሉ እንስት ተዋናይቶች ዝና መናኘት ጀመረ፡፡ ካምፑ በተከፈተ የመጀመሪያ ቀን ከቀድሞው አስቸጋሪ ወቅት አንጻር የነበረው ልዩነት ወለል ብሎ ታየ፡፡ በቀጣዮቹ አስራ አምስት ቀናት ደግሞ ከስፖርቱ ዘርፍ ቶተንሃም ሆትስፐር፣ ማንችስተር፣ ሬንጀርስና ቦልተን ዎንደረርስን የመሳሰሉ ቡድኖች ጥሪ ተደረገላቸው፡፡ ኮኽን ያን ጊዜ ሲያስታውስ ” የሚካሄደው አንድ የኳስ ጨዋታ ብቻ ነበር፡፡ የጎል ቋሚዎች ደግሞ ምሰሶ ላይ በተንጠለጠሉ ጃኬቶች ይሰሩ ነበር፡፡ የሆነ ወቅት ላይ የካምፑ አለቃ ጄነራል ቮን ኬስል የጨዋታዎቹን መደረግ ተቃወመ፡፡ ስለዚህም በክረምቱ መጀመሪያ ላይ ይካሄድ የነበረውና ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት የጀመረው የሊግ ውድድር እንዲቆም ተደረገ፡፡ በጸደይ ወቅት ግን የቮን ኬስል ልብ መለስ አለልን፤ ከካምፑ ትይዩ በሚገኘው ሰፊ ቦታ ላይ ሁለት የእግርኳስ ሜዳዎች እንዲዘጋጁ አዘዘ፡፡ ፔንትላንድ፣ ብሉመርና ካሜሮን የሩኽልበን እግርኳስ ማህበርን አቋቋሙ፡፡ የመጀመሪያ ግጥሚያቸውንም የራሳቸውን ደንብና መመሪያ ተጠቅመው በብሉመር አምበልነት የሚመራውና ሩኽልበንን በሚወክለው ቡድን እና በሚስተር ሪቻርድስ አማካኝነት በተወከለው ቀሪው የእስረኞች ቡድን መካከል በሚያዝያ 29-1915 ተካሄደ፡፡ ” በዚህ ጨዋታ የታየው ድባብ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች በቂ ልምምድ ከውነው እግርኳሱ ደረጃውን የጠበቀ ይዘት እንዲላበስ የተሻለ ጥረት ተደረጓል፡፡” ሲል በካምፑ የሚታተም መጽሄት ስለጨዋታው ዘገበ፡፡ በግንቦት 2-1915 ፔንትላንድ፣ ዎልስተንሆልምና ብሉመርን ያካተተው የእንግሊዝ ምርጥ አስራ አንድ በካሜሮን አምበልነት የሚመራውን የአለም ምርጥ አስራ አንድ ገጠመ፡፡ አስራ አራቱም የወታደር ሰፈሮች እያንዳንዳቸውን የሚወክሉ ሁለት ቡድኖች በሊግ እርከን ውስጥ አካተቱ፡፡ ብልሃት የተላበሰ የፉክክር መድረክም ተፈጠረ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ታዳሚዎችን መሳብ የቻለ መደበኛ ውድድር ተጀመረ፡፡
ይቀጥላል...
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
–Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
–Sunderland: A Club Transformed (2007)
–Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
–The Anatomy of England (2010)
–Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
–The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
–The Anatomy of Liverpool (2013)
–Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
–The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)