ከነገዎቹ ጨዋታዎች መካከል በቅድሚያ በዳሰሳችን የምንመለከተው የድቻ እና የቡናን ጨዋታ ይሆናል።
ለወራጅ ቀጠናው ቀርቦ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት የ20ኛ ሳምንት ጨዋታ ነገ ሶዶ ላይ በ 09፡00 ይከናወናል። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻለ ንቃት የሚታይባቸው ወላይታ ድቻዎች ሳምንት የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ሽንፈት መቐለ ላይ አስተናግደዋል። ለአራት ሳምንታት ያለሽንፈት መጓዝ ችለው የነበሩት የጦና ንቦቹ አሁን ላይ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀት ብቻ ከፍ ብለው ነው የተቀመጡት። በመሆኑም ከነገው ጨዋታ የሚገኙት ነጥቦች ከአደጋ ለመራቅ በእጅጉ የሚያግዟቸው በመሆኑ ሜዳቸው ላይ እስካሁን ያልተረቱት ድቻዎች በሙሉ ኃይላቸው ለማጥቃት እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ላይ እምብዛም ለውጥ እያደረጉ የማይገኙት ድቻዎች ኳስ መሀል ላይ ይዘው በመንቀሳቀስ ለባዬ እና አላዛር ጥምረት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክሩበት ሂደት በተሻለ የራስ መተማመን ጥሩ መግባባት ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል። በነገው ጨዋታ በተለይም በድኑ በመስመር አማካዮቹ በኩል የተጋጣሚውን የመከላከል የግራ እና የቀኝ ክፍል የሚፈትንበት ዕድል እንዳለው ይታመናል። በዚህ ሂደት ውስጥም ተሻሽሎ ሊቀርብ ከሚችለው የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ጋር የሚኖረው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው። በጨዋታው ወላይታ ድቻ ወደ መቐለ በጉዳት ሳቢያ መጓዝ ያልቻሉት ውብሸት ክፍሌ ፣ ውብሸት አለማየሁ እና ሄኖክ አርፊጮን አገልግሎት ያገኛል።
ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ በወልዋሎ እና ደደቢት ላይ ካሳኳቸው ድሎች በኋላ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል። ጨዋታው ከዚህም በላይ ብዙ ብልጫ ተወስዶባቸው የተጠናቀቀ በመሆኑ በሁለቱ ድሎች በመመለስ ላይ የነበረው በራስ መተማመናቸውን እንዳይሸረሽረው ያሰጋል። በፋሲሉ ጨዋታ ላይ የነበሩት ደካማ ጎኖች መሻሻል ካላሳዩም የድቻው ጨዋታ ለቡድኑ ከባድ የሚሆን ይመስላል። መሀል ላይ የተጋጣሚን ቅብብሎች በቶሎ ለማቋረጥ አለመቻል እንዲሁም ለአጥቂዎች በቂ የግብ ዕድሎችን አለመፍጠር ቡድኑ ላይ በሰፊው ተስተሏል። የማጥቃት ፍላጎቱ በተጠና መንገድ ይከውን ያነበረ በመሆኑም ኳስ በሚነጠቅበት ወቅት ከኋላ ለመልሶ ማጥቃት እጅግ የተመቹ ክፍተቶችን ሲተው ይታይ ነበር። ይህ ደግሞ በሰሞኑ ጨዋታዎች ኳስን መስርቶ በትዕግስት ለማጥቃት ሲሞክር ለሚታየው ወላይታ ድቻ የግብ ዕድሎችን መፍጠሪያ አማራጮች ሊፈጥርለት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። በርግጥ የአማኑኤል ዮሀንስ ከጉዳት መመለስ መሀል ላይ ቡድኑ የተሻለ ኳስ የማቋረጥ ጥንካሬን ሊያላብሰው ቢችልም የፊት አጥቂዎቹን በተለይም ጥሩ ሆኖ የሚታየው ሁሴን ሻቫኒ እና አቡበከር ነስሩን በመጨረሻ ኳሶች የሚያግዝ እንቅስቃሴ ከቡድኑ ይጠበቃል። አምበሉን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ቡና በፋሲሉ ጨዋታ የተጎዳው ክሪዚስቶም ንታንቢ እንዲሁም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ዋቴንጋ ኢስማ ፣ ተመስገን ካስትሮ እና ሚኪያስ መኮንን የማይጠቀም ይሆናል።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ11 ጊዜያት ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ጊዜ ወላይታ ድቻ ደግሞ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተለያዩ ሲሆን ቡና ዘጠኝ ድቻ ደግሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።
– ሶዶ ላይ ሽንፈት ያላገኘው ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በሜዳው ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች አራቱን በድል አራቱን ደግሞ በአቻ ውጤቶች አጠናቋል። በአጠቃልይ ውድድሩም ድል የቀነው በሜዳው ላይ ጨዋታዎቹ ብቻ ነው።
– ሰባት ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታድየም ውጪ ጨዋታዎቹን ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና ሁለት የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ሦስት ጊዜ ተሸንፏል።
ዳኛ
– ጨዋታው በኢንተናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን የሚመራ ስምንተኛ ጨዋታ ነው። ኢትዮጵያ ቡናን ከመከላከያ ያጫወተው እና ድቻን በያዝነው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዳኘው አርቢትሩ 28 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን እና አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ አሳልፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)
ታሪክ ጌትነት
እሸቱ መና – ደጉ ደበበ – ውብሸት ዓለማየሁ – ሄኖክ አርፌጮ
በረከት ወልዴ
ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ቸርነት ጉግሳ
ባዬ ገዛኸኝ – አላዛር ፋሲካ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
ወንድወሰን አሸናፊ
አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ወንድይፍራው ጌታሁን – እያሱ ታምሩ
አማኑኤል ዮሀንስ – ሄኖክ ካሳሁን – ካሉሻ አልሀሰን
አስራት ቱንጆ – አቡበከር ናስር – ሁሴን ሻቫኒ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡