አአ U-17 | ቅዱስ ጊዮርጊስ በግስጋሴው ሲቀጥል ሌሎች ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል


የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 7ኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ የአሸናፊነት ጉዞው ሲቀጥል ሌሎቹ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

03:00 በአካዳሚ ሜዳ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ አፍሮ ፅዮን ከሀሌታ ጋር ሁለቱም በፍፁም ቅጣት ምት ባስቆጠሯቸው ጎል አንድ አቻ በሆነ ውጤት ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ከሰንጠረዡ ግርጌ ለመውጣት የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር፣ ሳቢ የሆነ አጨዋወት ይካሄድበታል ተብሎ ቢጠበቅም ቀዝቅዞ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ጎል አስቀድመው ያስቆጠሩት አፍሮ ፅዮኖች በፍ/ቅ/ምት ፉአድ ቢንያም ሲሆን ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ ይስሐቅ መኩርያ በፍ/ቅ/ምት ለሀሌታ ጎል አስቆጥሮ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

05:00 በዚሁ በአካዳሚ ሜዳ በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ አካዳሚ ከሦስት ባዶ መመራት ተነስቶ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሦስት አቻ ተለያይቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ከቅጣት ምት የተሻማ ኳስ ግብ ጠባቂ ሲተፋው የመሀል ተከላካዩ ቢኒያም ጎዳና በጭንቅላት ገጭቶ ቡናዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከእረፍት መልስ በሚኪያስ ቡልቡላ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በአካዳሚ ተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ሳጥን ውስጥ ያገኝውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ቡናዎች ሁለተኛ ጎል ሲያስቆጥር በድጋሚ ከደቂቃዎች በኋላ ቢኒያም ቡልቡላ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ከግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ወደግብነት በመቀየር ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

አካዳሚዎች ሰኬታማ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ተቀይሮ የገባው አብዱልፈታህ ሃሚድ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደግብ በመቀየር አካዳሚዎች ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ እንዲገቡ ማድረግ ችሏል። ይበልጥ አጥቅተው የተጫወቱት አካዳሚዎች ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ይዞት የገባውን ኳስ ከድር ዓሊ አስቆጥሮ የጎል መጠኑን ሲያጠብ ይበልጥ የተሻለ አጥቅተው የተጫወቱት አካዳሚዎች አብዱልፈታህ ሃሚድ ከመሀል የሾለከለትን ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር በመገናኝት ወደግብ በቀየረው ኳስ በድራማዊ ትዕይት 3-3 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

04:00 በጎፋ ሜዳ በተካሄደ ሌላ ጨዋታ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከሠላም አገናኝቶ በፈረሰኞቹ የበላይነት 5-0 ተጠናቋል።

ገና በጨዋታው ጅማሬ ጊዮርጊሶች በአምበሉ እዮብ መርሻ ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም በእንቅስቃሴ ረገድ ሠላሞች የተሻሉ መሆን ችለዋል። ሆኖም በፊት መስመር ላይ ያሉት አጥቂዎች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ባለመቻላቸው ብልጫቸውን በአግባቡ መጠቀምገአልቻሉም። ከቅጣት ምት አላዛር ሳሙኤል ግሩም ሁለተኛ ጎል ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስቆጥሮም ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በየጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ እየሆነ የመጣው እና የሠላም ተከላካዮች መቆጣጠር ያቃታቸው ፀጋዬ መላኩ በደቃቃዎች ልዩነት የግል ክህሎቱን በመጠቀም ሦስተኛ እና አራተኛ የቡድኑን ጎል አስቆጥሮ የፈረሰኞቹን የጎል መጠን ወደ አራት ከፍ ሲያደርግ እስካሁን በውድድሩ ያስቆጠረውን የጎል መጠን ወደ 11 በማሳደግ ኮከብ ጎል አስቆጣሪነትን መምራትም ችሏል። ጨዋታው ቀጥሎ ተቀይሮ የገባው ዘይኑ ሽኩር አምስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል እስካሁን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ በመጫወት አስገራሚ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኘው የተከላካይ አማካዩ ፉአድ ሀቢብ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን ከወዲሁ መናገር ይቻላል።

06:00 በጎፋ ሜዳ የተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር ሲስተዋልበት በታየው በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ በበላይነት መቆጣጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ መከላከያዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከእረፍት መልስ ያሬድ ማቴዮስ ለመከላከያ ጎል አስቆጥሮ መምራት ቢችሉም ለኢትዮ ኤሌትሪክ አንዋር ሙራድ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። በሁለቱም በኩል ጥሩ የጎል አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ቢቸገሩም የመከላከያው አጥቂ ውጤት ዓለማየሁ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ መምራት ሲችሉ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጫና የፈጠሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተቀይሮ በገባው ዳዊት ሲሳይ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው 2-2 አቻ በሆነ ውጤት ተፈፅሟል።

በኤሌትሪኮች በኩል የመስመር አጥቂ በመሆን ቡድኑ ጥሩ በሆነበትም ጥሩ ባልሆነበትም ጊዜ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለተቃራኒ ቡድን ፈተኛ የሆነው እና የእግርኳስ መነሻውን ያደረገው በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር የሆነው ይበልጣል ቻሌ ወደ ፊት ተስፋ የሚደረግበት ታዳጊ ተጫዋች መሆኑን በእንቅስቃሴው መታዘብ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡