ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ደቡብ ፖሊስ

ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት የፋሲል እና የደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ነው።

የጎንደሩ ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም በ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የፋሲል እና ደቡብ ፖሊስን ጨዋታ ያስተናግዳል። በሳምንቱ መግቢያ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት ፋሲሎች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ቢገደዱም በጨዋታው ያሳዩት አቋም ግን ለቀጣይ ጉዟቸው እጅግ የሚያነሳሳ ነው። ከዚያ አስቀድሞ በነበረው የመቐለ ጨዋታ ከሚካላከል ቡድን ጋር በቡናው ጨዋታ ደግሞ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ከሚያደርግ ቡድን ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች የተለያየ ፈተና ቢገጥማቸውም በአመዛኙ ስኬታማ ነበሩ ማለት ይቻላል። ኳስ ለመመስረት የተመቸ እና በማጥቃት ላይ የሚሳተፍ የኋላ ክፍል፣ በቀላሉ ኳስ የማይነጠቅ የተረጋጋ የማካይ ክፍል እንዲሁም ታታሪ የመስመር አጥቂዎች ጥምረቱ በተጋጣሚዎቹ ላይ ብልጫ ለመውሰድ እና የግብ ዕድሎችን በብዛት መፍጠር ከብዶት አልታየም። ሆኖም የመጨረሻ ዕድሎችን ደጋግሞ ማምከኑ ትልቁ ጉድለቱ ሆኗል። በነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ አካሄድ ከአፄዎቹ የሚጠበቅ ሲሆን ተጋጣሚያቸው በመስመር በኩል በማጥቃቱ ጠንካራ በመሆኑ ግን የመስመር ተከላካዮቻቸው የማጥቃት ሚና ሊገደብ ይችላል። አብዱራህማን ሙባረክ እና ኤፍሬም አለሙን ከጉዳት መልስ የሚያገኙት ዐፄዎቹ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸውን ወደ ሦስት ቀንሰው ይበልጥ ማጥቃት ላይ ትከረት አድርገው ወደ ሜዳ የሚገቡበትም ዕድል ሊኖር ይችላል።

ከአራት ተከታታይ ድሎቹ በኋላ ዳግም ወደ ውጤት ማጣት የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ ከደደቢት እና ወልዋሎ ሽንፈት በኋላ ነው ወደ ከባዱ የጎንደር ጨዋታ የሚያመራው። በአስገራሚ መልኩ የአጨዋወት ሂደቱ እና በራስ መተማመኑ ተሻሽሎ ይታይ የነበረው የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን ዳግም ከገባባት ወራጅ ቀጠና ለመውጣት እንዲረዳው ከማስቻል ባለፈ ዳግም የአሸናፊነት መንፈሱን ለማግኘት መሰል ትልቅ ጨዋታዎችን በድል ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል። አጥቅቶ የመጫወት ድፍረቱ ያላቸው ደቡብ ፖሊሶች ነገም በዋነኝነት የመስመር አጥቂዎቻቸውን ፍጥነት በመጠቀም በፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት እንደሚሞክሩ ይገመታል። ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት ከማሻገር ባለፈ ግን የቡድኑ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች የፋሲል አቻዎቻቸውን የማቆም ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በሌላ በኩል ከተጋጣሚያቸው ወቅታዊ አቋም አንፃር በተሸነፉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ደቡብ ፖሊሶች ወደ ጥንቃቄ አድልተው ነጥብ መጋራትንም የዕቅዳቸው አካል ሊያደርጉ ይችላሉ። በጨዋታው ደቡብ ፖሊሶች አማካዩ ኤርሚያስ በላይ ረዘም ካለ ጉዳት የሚመለስላቸው ሲሆን አበባው ቡጣቆ በቅጣት አዳሙ መሀመድ ደግሞ ከክለቡ ጋር በተፈጠረ አለመስማማት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ዘንድሮ ከ2000 በኋላ በፕሪምየር ሊጉ የተገናኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ተከናውኖ ፋሲል በኢዙ አዙካ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

– ፋሲል ከነማ ሜዳው ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎች አድርጎ ስድስት ድሎች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቧል። እስካሁን ጎንደር ላይ ሽንፈት ያላገኘው ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አምስት የሜዳው ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም።

– ከስምንት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአምስቱ ሽንፈት የገጠመው ደቡብ ፖሊስ ሁለቴ አሸንፎ ሁለት ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተመልሷል።

ዳኛ

– ፋሲል ከነማን ከወላይታ ድቻ ያጫወተው ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ ይመራዋል። ተካልኝ እስካሁን በሰባት ጨዋታዎች 25 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ሲመዝ ሁለት ተጫዋቾችን በሁለተኛ ቢጫ ካርድ አስወጥቶ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቷል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚኬል ሳማኬ

ሰዒድ ሁሴን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ኤፍሬን ዓለሙ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ

ደቡብ ፖሊስ (4-3-3)

ሐብቴ ከድር

አናጋው ባደግ – ደስታ ጊቻሞ – ዘሪሁን አንሼቦ – ዘነበ ከድር

ዘላለም ኢሳያስ – ዮናስ በርታ – ኪዳኔ አሰፋ

የተሻ ግዛው – ኄኖክ አየለ – በረከት ይስሀቅ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡