የ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር ባህር ዳር ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር የታየበት የአውስኮድ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ሰባት ጎሎች ተስተናግደውበት በእንግዶቹ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ተጋባዦቹ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተለይ በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር ተረጋግተው ተጫውተዋል። በተቃራኒው ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የገቡት ባለሜዳዎቹ አውስኮዶች በ11ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ የቡድኑ አምበል መልካሙ አለሙ ያሻገረው የመዓዘን ምት ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው ሐቁምንይሁን ገዛህኝ አክርሮ በመምታት ግብ አስቆጥሯል።
ጨዋታውን እንደመቆጣጠራቸው በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ያልቻሉት ኤሌክትሪኮች አጨዋወታቸውን በመስመር ላይ በማድረግ ወደ ግብ ለመቅረብ ሞክረዋል። በዚህም በ16ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ወንድማገኝ አብሬ በግምባሩ ሞክሮ በመከነበት ኳስ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። የተከላካይ መስመር ተጨዋቾቻቸውን ወደ መሃል ሜዳ አስጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ኤልፓዎች ከጀርባቸው ትተውት በሚወጡት ሰፊ ቦታ አማካኝነት ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ሲፈጠርባቸው ተስተውሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሚካኤል ጆርጅ ከተከላካዮቸ ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ለቀፀላ ፍ/ማርያም አቀብሎት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉበትን አጋጣሚ ቀፀላ አምክኖታል። በቀኝ መስመር በኩል አድልተው ሲያጠቁ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በ20ኛው ደቂቃ በተገኘ ያልታሰበ አጋጣሚ አቻ ሆነዋል። ቢኒያም ትዕዛዙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የአውስኮድ ግብ ጠባቂ ዘውዱ መስፍን ተረጋግቶ በእግሩ ከተቆጣጠረው በኋላ ለውሳኔ በመዘግየቱ በአጋማሹ ከቢሾፍቱ ክለቡን የተቀላቀለው ወንድማገኝ አብሬ ቀምቶት ወደ ግብነት ቀይሮታል። ያልተጠበቀ ግብ የተቆጠረባቸው አውስኮዶች በ25ኛው ደቂቃ ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ ለቀፀላ አመቻችቶ ባቀበለው ነገር ግን ቀፀላ ባመከነው ኳስ ይበልጥ ለግብ ቀርበው ነበር።
አሁንም በቀኝ በኩል ጥቃት መሰንዘራቸውን የቀጠሉት ተጋባዦቹ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ቢኒያም ትዛዙ አማካኝነት የተሻገረን ኳስ ስንታየሁ ዋለጬ በ31ኛው ደቂቃ በግምባሩ አስቆጥሮ መሪ ሆነዋል። ከዚህች ግብ በኋላ የተቀዛቀዙት አውስኮዶች እስከ እረፍት ድረስ በምንም አይነት አጋጣሚ ወደ ኤሌክትሪኮች የግብ ክልል ሳይደርሱ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጥሩ ፉክክር ሲስተዋልበት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክሮ አራት ጎሎች ተቆጥረውበታል። አጋማሹ ገና እንደተጀመረም ታፈሰ ተስፋዬ ከመስመር ላይ ያገኘውን ኳስ ለወንድማገኝ አብሬ አቀብሎት ወንድማገኝ ባልተጠቀመበት ኳስ ኤሌክትሪኮች ግብ ለማስቆጠር ሲቃረቡ በተቃራኒው አውስኮዶች ደግሞ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በኃይሉ ወልዴ ከግራ መስመር ባሻማው ነገር ግን ሚካኤል ጆርጅ ባመከነው ኳስ ገና በጅማሮ ግብ ሲፈልጉ ታይቷል። ጥረታቸው ጥሩ ምላሽ ያመጣላቸው አውስኮዶች በ52ኛው ደቂቃ በግርማ ፅጌ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ ሆነዋል። ኤሌክትሪኮች የአቻነቷን ግብ ከተቆጠረችባቸው ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ግብ አስቆጥረው ድጋሚ መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ የደረሱት የአሰልጣኝ አንዋር ተጨዋቾች አጋጣሚውን በወንድማገኝ አብሬ አማካኝነት ወደ ጎልነት ቀይረውታል።
ተመልካችን ቁጭ ብድግ በማድረግ የቀጠለው ጨዋታው በ62ኛው ደቂቃ በተፈጠረ አጋጣሚ ግብ ለማስተናገድ እጅጉኑ ተቃርቦ ነበረ። ሚካኤል ጆርጅ ከመሃል ሜዳ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብ በመሄድ የሞከረው ሙከራ የግቡን መረብ ነክቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጥረታቸውን ያላቋረጡት አውስኮዶች በ66ኛው ደቂቃ መላኩ ፈጠነ በግምባሩ ባስቆጠረላቸው ኳስ ድጋሚ ወደ ጨዋታው ተመልሰው አቻ ሆነዋል።
የአቻነት ጎል ካስቆጠሩ በኋላም ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲያመክኑ የተስተዋሉት አውስኮዶች በስተመጨረሻ ዋጋ ከፍለው የተሸነፉበትን ግብ አስተናግደዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀረው ተቀይሮ የገባው መሐመድ ጀማል ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ለታፈሰ ተስፋዬ ያቀበለውን ኳስ አንጋፋው አጥቂ በጥሩ ሁኔታ ከመረብ አገናኝቶ ለሶስተኛ ጊዜ መሪ ሆነዋል። አውስኮዶች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡