በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ፀጋዬ አበራ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ታግዞ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በመቐለ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስቡ ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ ከፋሲል ከነማ ጋር በሜዳው ነጥብ ተጋርቶ የመጣው ኢትዮጵያ ቡና የሶስት ተጫዋቾች ለውጥን በማድረግ ክሪዝስቶም ንታንቢ፣ አማኑኤል ዮሐንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ከአሰላለፉ በማውጣት በምትኩ ቶማስ ስምረቱ፣ ተካልኝ ደጀኔ እና አልሀሰን ካሉሻን ተጠቅመዋል፡፡
እጅጉን ቅርፅ አልባ የሜዳ ላይ የጨዋታ ሂደትን በተመለከትንበት የመጀመሪያው አጋማሽ አጀማመራቸው መልካም የነበረው ኢትዮጵያ ቡናዎች ገና በጊዜ በግራ አቅጣጫ አቡበከር ነስሩ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘን ቅጣት ምት ተካልኝ ደጀኔ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ታሪክ ጌትነት መቆጣጠር ሳይችለው በድጋሚ ስትመለስ አቡበከር ለጥቂት ባመለጠችው ጠንካራ አጋጣሚ ቀዳሚ የጨዋታ ሙከራን ማድረግ ቢችሉም በወላይታ ድቻ ቀስ በቀስ ብልጫ ሊወሰድባቸው ችሏል፡፡ በዚህም እሸቱ መና ከግብ ክልል በረጅሙ የላከለትን ኳስ ፀጋዬ አበራ ተቆጣጥሮ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት የፈጠረው እና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ተጠቃሽ ሙከራ ናት ፡፡
የወላይታ ድቻን ረጃጅም ኳስ መጠቀምን የተመለከቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ተመሳሳይ መንገድን ለመከተል ተገደዋል። በተለይ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሁሴን ሻባኒን ማዕከል ያደረጉ ጥቃቶችን ቢያገኙም የመጨረሻው የኳስ ማረፊያ ግን ስኬታማ አልነበረም፡፡ ሁሴን ሻባኒ 23ኛው ደቂቃ ላይ ወደ መሀል ሜዳው ተስቦ በመምጣት በግል ጥረቱ እየነዳ ወደ ድቻ የግብ ክልል ደርሶ ለአቡበከር ሰጥቶት አቡበከር በጥሩ ሁኔታ ለኢያሱ ቢሰጠውም ኢላማዋን ያልጠበቀች ጥሩ ዕድልን አግኝቶ አምክኗታል፡፡
34ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታን የመጀመሪያ ግብ መመልከት ችለናል፡፡ ከማዕዘን ምት እሸቱ መና ሲያሻማ ፀጋዬ አበራ በግንባር ገጭቶ ወላይታ ድቻን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ግቧን ፀጋዬ ሲያስቆጥር ግቡ ጠባቂው ወንደሰን አሸናፊ ላይ ጥፋት ሰርቷል ግቧ መፅደቅ የለባትም በሚል ኢትዮጵያ ቡናዎች በዳኛው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን የእለቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነ ብርሀን ላይ ክስ አስመዝግበዋል። ግብ ጠባቂው ወንደሰን አሸናፊም ህክምና ተደርጎለት ከስምንት ደቂቃ መቋረጥ በኃላ ጨዋታው በድጋሚ ቀጥሏል፡፡ 42ኛው ደቂቃ ላይ አትዮጵያ ቡናዎች በአቡበከር ነስሩ አማካኝነት ከቅጣት ምት በተገኘች ኳስ ለማስቆጠር የተቃረቡ ቢመስሉም ግብ ሳይቆጠር በጦና ንቦቹ 1-0 መሪነት እረፍት ወጥተዋል፡፡
ከእረፍት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ የታየባቸው ድክመት ለማረም የሚመስል እንቅስቃሴን ገና በጊዜ በግብ መከራ እና በግብ አጅበው ጅማሮን አድርገዋል፡፡ 48ኛው ደቂቃም አቡበከር በአስደናቂ መልኩ በግራ በኩል ለካሉሻ ሰጥቶት ካሉሻ ወደ ግብ ክልል ገብቶ ከግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው በግሩም ሁኔታ ባስጣለው ኳስ ድቻዎችን መፈተን ጀምረዋል፡፡ ብዙም ሳይቆይ 56ኛው ደቂቃ በወላይታ የቀኝ የግብ መስመር ላይ እሸቱ መና እና ፀጋዬ አበራ ኳሱን ከራሳቸው አካባቢ ለማረቅ ሲገባበዙ ሁሴን ሻባኒ በፍጥነት ደርሶ ነጥቋቸው ለኢያሱ ሰጥቶት እያሱ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ካሉሻ ያቀበለውን ጋናዊው አማካይ ወደ ግብነት ለውጧት ቡናን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ግብ ካስቆጠሩ በኃላ መነቃቃት የታየባቸው ቡናማዎቹ ቢሆኑም አሁንም ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀም ላይ ትኩረትን ያደረጉት ድቻዎች በአንፃሩ በተሻለ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ጎልተው ወጥተዋል፡፡ ሻባኒ ቶሎ ቶሎ በሚያገኘው ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ከሱ ጋር በቅብብሎሽ ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚችሉ ተጫዋቾች ባለመኖራቸው ሲባክን አስተውለናል፡፡ 76ኛው ደቂቃ በአህመድ ረሺድ ጥረት የተገኘችውን የማዕዘን ምት ኢያሱ አሻምቶ ሄኖክ ካሳሁን በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ወታበታለች፡፡
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ብልጫን የወሰዱት ድቻዎች በቅያሬያቸው ታግዘው ሙሉ ሶስት ነጥብን አሳክተዋል፡፡ በአብዛኛው በመከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወትን የሚከተሉትን አንተነህ ጉግሳ አብዱልሰመድ ዓሊን እንዲሁም በጨዋታው ብዙም ልዩነት መፍጠር ያልቻለው አላዛር ፋሲካን አስወጥተው ሄኖክ አርፊጮ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ኃይሌ እሸቱ በምትኩ ወደ ሜዳ በማስገባት በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ቡናዎች የግብ ክልል አድልተው መጫወት የጀመሩት የጦና ንቦቹ 81ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ ቸርነት ጉግሳ በቀኝ በኩል የማዕዘን መምቻው ጋር ሁሴን ሻባኒን አልፎ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባሩ ገጭቶ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛዋን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል ። ግቧ ስትቆጠር ወንደሰን አሸናፊ ከእጁ አምልጣ ከመስመር ካለፈች በኃላ ዋናው እና ረዳት ዳኛው ያፀደቁት ቢሆንም ወንደሰን እና ተጫዋቾቹ በድጋሚ በዳኛው ላይ ቅሬታን አሰምተዋል፡፡
በጭማሪው ደቂቃ (90+4 ላይ) ከጨዋታ ውጪ በማለት ዳኛው ፊሽካቸውን ካሰሙ በኃላ ባዬ ገዛኸኝ የዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ኳሷን በመለጋቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ክስተት ሳይታይበት በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ከማለቂያው በኋላም ዳኛው ላይ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተመልክተናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡